ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የለያቸው አጀንዳዎች የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሀሳብ ያካተቱ ናቸው

ሮቤ፣ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የለያቸው አጀንዳዎች መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉና አካታች መሆናቸውን የሮቤ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ኮሚሽኑ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ማካሄድ ለሚጀምረው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚቀርቡ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን መለየቱ ይታወሳል።

በኮሚሽኑ የተለዩትን አጀንዳዎች በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎችና የሥራ ኃላፊዎች፤ የተመረጡት አጀንዳዎች የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉና ሁሉንም አካታች ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የዋቆ ጉቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደሳለኝ አብደታ፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የነበሩ አለመግባባቶችን መፍታት ያስችላል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በምክክር ኮሚሽኑ የተለዩት ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉና አካታች በመሆናቸው፣ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የባሌ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባልደረባ አቶ አበባ ገላልቻ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን ሰብስቦ አካታች በሆነ መልኩ ለምክክር ያቀረበበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለምክክር ሂደቱ ውጤታማነት በተለያዩ መድረኮች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

መምህር ጸጋዬ በየና በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት ፈትቶ አብሮነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሂደት የኢትዮጵያን የቆዩ ችግሮች በምክክር ለመፍታት የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን በመረዳት፣ ለውጤታማነቱ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ገረመው ከፍያለሁ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ሀሳብ በመቀበል መሰረታዊና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር የለያቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች አካታችና ከዚህ በፊት የነበሩ ቁርሾዎች እንዲፈቱ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም፣ የኮሚሽኑ የእስከ አሁኑ ሂደት የሀሳብ ፍትሃዊነትና አካታችነት የሰፈነበት መሆኑን በመረዳት ለውጤታማነቱ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም