ከለውጡ በኋላ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለልማት ስኬት ፅኑ መሰረት እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከለውጡ በኋላ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለልማት ስኬት ፅኑ መሰረት እየሆነ ነው
ሃዋሳ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ):- ከለውጡ በኋላ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለልማት ስኬት ጽኑ መሰረት መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርሻቸውን ተወጥተዋል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያደረጉት ቅንጅታዊ ስራ ለምርጫው ስኬት ጉልህ ድርሻ ነበረው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አጠቃላይ ህዝቡም ለሰላምና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለልማት ስኬት ፅኑ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በለጠ ሲጌቦ፤ በተፈጠረው ምቹ እና አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር በክልሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ለምርጫው ስኬት የጋራ ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱን ጠቅሰው የዛሬው መድረክ ዋና አላማም ለስኬቱ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን እውቅና መስጠት ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ 24 የፖለቲካ ፓርቲዎች አብላጫ መቀመጫ በማግኘቱ መንግስት ከሚመሰርተው ብልጽግና ፓርቲ ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራና በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ኤርሚያስ፤ በክልሉ የተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገረ መንግስት ግንባታው ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጋራ ምክር ቤቱ የበኩሉን ድርሻ ማበርከቱን ጠቅሰው በቀጣይም ከመንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
በመድረኩ የጋራ ምክር ቤቱ በቅድመ ምርጫ በምርጫ እለትና በድህረ ምርጫ ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለምርጫው ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።