ቀጥታ፡

ዩኒቨርስቲው በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው

አሶሳ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ አሶሳ ዩኒቨርስቲ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች በክህሎት የታነፀ ትውልድ ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርስቲው በ13ኛ ዙር በመደበኛ፣ በተከታታይ እና በክረምት መርሃግብር ያስተማራቸውን 673 ተማሪዎች አስመርቋል።


 

የአሶሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ያሬድ ሙሉ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርስቲው በተግባር ተኮር ሳይንስ ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የምርምር ስራዎችን በማከናወን አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው።

በተለይም በግብርና፣ እና በማዕድን ዘርፍ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን በማውጣት የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታነፀ እና በክህሎት የበለፀገ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች ሀገሪቱ ለምትፈልገው የተማረ የሰው ሀይል ተጨማሪ አቅም ይሆናሉ ብለዋል።


 

ተመራቂዎች ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የብልጽግና ጉዞ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም ነው ያሳሰቡት።

በመርሃ ግብሩ ላይ በባህልና ስፖርት ሚኒስትር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሀዲ፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም