ቀጥታ፡

ሴኔጋል ጥሎ ማለፉን ተቀላቀለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ ሰባት የመጨረሻ ጨዋታዎች ማለዳ ላይ ተደርገዋል።

በቢሲ ፕሌስ ቫንኩቨር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቤልጂየም ኒውዝላንድን 5 ለ 1 ረታለች።

ሊያንድሮ ትሮሳርድ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኬቨን ደ ብሮይን፣ ሮሜሎ ሉካኩ እና አሌክሲስ ሳሌማከርስ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ሉካኩ በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ስድስት አድርሷል።

ኤሊጃህ ጀስት ለኒውዝላንድ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ውጤቱን ተከትላ ቤልጂየም በአምስት ነጥብ ምድቡን በመሪነት በማጠናቀቅ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

ኒውዝላንድ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ በመያዝ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

በሲያትል ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር ግብጽ እና ኢራን አንድ አቻ ተለያይተዋል።

መሐሙድ ሳቡር ለግብጽ፣ ራሚን ሬዛያን ለኢራን ግቦቹን አስቆጥረዋል።

አስቀድማ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷን ያረጋገጠችው ግብጽ በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ኢራን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በምርጥ ሶስተኛነት ለማለፍ የቀሪ የምድብ ጨዋታዎችን ውጤቶች ትጠብቃለች።

የምድብ ስምንት ውጤቶችን ተከትሎ በምድብ ዘጠኝ በሶስት ነጥብ እና በሁለት የግብ ክፍያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ሴኔጋል በምርጥ ሶስተኝነት  ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።

ይህን ተከትሎም ወደ ጥሎ ማለፉ የገቡ የአፍሪካ ሀገራት ብዛት ሰባት ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም