ቀጥታ፡

ከአልጄሪያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ማን ወደ ጥሎ ማለፍ ያልፋል?

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ
መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።

በምድብ 12 ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ክሮሺያ ከጋና በፊላደልፊያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ክሮሺያ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ፣ ጋና በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የደቡብ ምስራቅ አውሮፓዊቷ ሀገር ክሮሺያ ማሸነፍ ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባታል። የአቻ ውጤት በምርጥ ሶስተኝነት ሊያሳልፋት የሚችልበት እድል አለ።

ጋና ትናንት የተደረጉ የምድብ ጨዋታዎችን ተከትሎ ጥሎ ማለፍ መግባቷን አረጋግጣለች።

በዚሁ ምድብ ፓናማ ከእንግሊዝ በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም በተመሳሳይ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ሁለት ጊዜ የተሸነፈችው ፓናማ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

በአራት ነጥብ ምድቡን እየመራች የምትገኘው እንግሊዝ የትናንት ውጤቶችን ተከትሎ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብታለች።

በሌላ በኩል በምድብ 10 የምትገኘው አልጄሪያ ከኦስትሪያ ጋር ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ኦስትሪያ እና አልጄሪያ በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የጨዋታው አሸናፊ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱን ያረጋግጣል። አቻ መውጣትም ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያሳልፋቸው የሚችልበት እድል አለ።

የምድቡ መሪ አርጀንቲና ከጆርዳን ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ በዳላስ ስታዲየም ጋር ትጫወታለች።

አርጀንቲና በስድስት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷ ይታወቃል። ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት የምድቡ መሪ ሆና እንድታጠናቅቅ ያስችላታል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ላይ እየተሳተፈች የምትገኘው ጆርዳን ሁለት ጊዜ ተሸንፋ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

በተያያዘም የምድብ 11 የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኡዝቤኪስታን ከሌሊቱ 8 ሰዓት ከ30 በአትላንታ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

የማዕከላዊ  አፍሪካዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።  ኡዝቤኪስታን ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻው አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኮንጎ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ያላት ብቸኛ እድል ማሸነፍ ብቻ ነው።

በዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈች የሚገኘው ኡዝቤኪስታን ማሸነፍ በምርጥ ሶስተኝነት ወደ ጥሎ ማለፉ ሊያስገባት ይችላል።

በዚሁ ምድብ ኮሎምቢያ ከፖርቹጋል በተመሳሳይ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ከ30 ላይ በሚያሚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደሰርጋሉ።

ኮሎምቢያ በስድስት ነጥብ ከምድቧ ማለፏን አረጋግጣለች። ፖርቹጋል በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፍ መግባቷን አረጋግጣለች።

የደቡብ አሜሪካዋ ኮሎምቢያ ካሸነፈች ወይም አቻ ከወጣች የምድቡ መሪ ሆና ታጠናቅቃለች።

ፖርቹጋል ማሸነፍ የምድቡ መሪ ሆና እንድታጠናቅቅ ያስችላታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም