ተመራቂዎች የኢትዮጵያን የሪፎርም ጉዞ ይበልጥ ለማሳካት እና አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች የኢትዮጵያን የሪፎርም ጉዞ ይበልጥ ለማሳካት እና አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ተመራቂ ተማሪዎች የኢትዮጵያን የሪፎርም ጉዞ ይበልጥ ለማሳካት እና አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ2018 ዓ.ም በመደበኛ እና በተከታታይ የትምህርት መርሀ ግብሮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።
በዚህ የምረቃ መርሀ ግብር ላይ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የቦርድ እና የሴኔት አባላት፣ ተመራቂዎች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ተቋማዊ ሪፎርም እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት አገልግሎትን ለማዘመን እና ለዜጎች የተሳለጠ አሰራርን ለመዘርጋት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የአገር ግንባታ በብቁ የሰው ኃይል የሚረጋገጥ በመሆኑ ተመራቂዎች በኢትዮጵያ እየተደረገ የሚገኘውን የሪፎርም ጉዞ የበለጠ ለማሳካት እና አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመሆኑም ተመራቂዎች በታማኝነት አገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸው ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው ወቅቱን የዋጀና የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ 1 ሺህ 363 ወንዶች እና 454 ሴቶች በድምሩ 1 ሺህ 817 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ማስመረቁን ጠቅሰዋል፡፡
ተቋሙ በትምህርት ዘርፍ፣ በአጫጭር ሥልጠናዎች፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች የሀገሪቱን የፐብሊክ ሴክተር ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ከተከናወኑት ተግባራት መካከልም በተደረገው አገራዊ ጥናት መሰረት፣ በርካታ ተቋማዊ፣ አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ሪፎረሞች በተግባር እየተተገበሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።