የኢትዮጵያ ሕዝብና የጸጥታ መዋቅር ምርጫውን ፍጹም ሰላማዊ በማድረግ የእኩይ ኃይሎችን ከንቱ ምኞት አክሽፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብና የጸጥታ መዋቅር ምርጫውን ፍጹም ሰላማዊ በማድረግ የእኩይ ኃይሎችን ከንቱ ምኞት አክሽፈዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሕዝብና የጸጥታ መዋቅር ምርጫውን ፍጹም ሰላማዊ በማድረግ የእኩይ ኃይሎችን ከንቱ ምኞት ማክሸፋቸውን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሰላምና ደህንነት፣ የፖሊስና የሚሊሻ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በቅድመ ጥናት ግጭቶች ወደ ከባድ ደረጃ ሳይደርሱ መከላከል የሚያስችል ነባራዊ አውድ እየተፈጠረ ነው።
የሰላም ሚኒስቴር ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር ሰላም ግንባታና አብሮነት ዙሪያ የጋራ መግባባት በመፍጠር ውጤታማ ሥራ አከናውኗል ብለዋል።
ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ ዜጎች የምርጫ ካርድ ለማውጣት እንዳይመዘገቡ፣ በምርጫው ዕለትም ድምፅ እንዳይሰጡ ፕሮፓጋንዳ ይሠራባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥትና በጸጥታ መዋቅሩ ላይ እምነት በመጣል የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰድ የቀን ፀሐይ የሌሊት ቁር ሳይበግራቸው ድምፃቸውን ሰጥተዋል ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብና የጸጥታ አካላት በድህረ ምርጫ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚለውን እኩይ ፍላጎት ማክሸፍ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ዓለም የሚደመምባቸውን ለውጦች ማስመዝገቧንምኝ ገልጸዋል።
የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የጸጥታ ተቋማት በአንድ መድረክ መገናኘት እንደ አገር የተቀናጀና የተናበበ የጸጥታ አጠባበቅ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ብዝሃነት የሚንጸባረቅባት በመሆኗ እንደ የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የግጭት አፈታት ልምድን መቅሰም ያስችላል ብለዋል።
የጸጥታ ተቋማት ቅንጅት ከኢትዮጵያም አልፎ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ዋስትና እንደሚሆን ገልጸዋል።