ሴኔጋል ኢራቅን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈች - ኢዜአ አማርኛ
ሴኔጋል ኢራቅን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ ዘጠኝ መርሐ ግብር ሴኔጋል አራቅን 5 ለ 0 ረትታለች።
ማምሻውን በቶርንቶ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ፓፕ ጌይ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሀቢብ ዲያራ፣ ኢስማይላ ሳር እና ኢሊማን ንጃይ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አጥቂው ኢስማይላ ሳር በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ሶስት አድርሷል።
የኢራቅ ተከላካይ ሬቢን ሱላካ በ13ኛው ደቂቃ በቀይም ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
በዓለም ዋንጫው ዘጠነኛው ካርድ ሆኖም ተመዝግቧል።
ሴኔጋል በጨዋታው ላይ ከወሰደችው ብልጫ በተጨማሪ ቀይ ካርዱ ፍጹም የበላይነት እንዲኖራት አድርጓል።
ሴኔጋል በዓለም ዋንጫ ታሪክ በአንድ ጨዋታ በርካታ ግብ ያስቆጠረች (አምስት) የመጀመሪያ አፍሪካዊ ሀገር ሆናለቾ።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድሏን ያስመዘገበችው ሴኔጋል በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ሴኔጋል ምርጥ ሶስተኛ ሆና ለማለፍ የሌሎች ምድቦችን ውጤቶች ትጠብቃለች። ዛሬ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፏ ተስፋዋ እንዲጨምር አድርጓል።
ሁሉንም የምድብ ጨዋታዋን የተሸነፈችው አራቅ ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ከውድድሩ ተሰናብታለች።
በዚሁ ምድብ በቦስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፈረንሳይ ኖርዌይን 4 ለ 1 አሸንፋለች።
ኡስማን ዴምቤሌ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።
ይህም በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የተቆጠረ ሶስተኛ ሀትሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።
ዴዚሬ ዱዌ ለፈረንሳይ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቴሎ አስጋርድ የኖርዌይን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።
የኖርዌዩ ጆርገን ስትራንድ ላርሰን በ50ኛው ደቂቃ ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ፈረንሳይ በዘጠኝ ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቃለች።
ፈረንሳይ ከሜክሲኮ በመቀጠል ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎቿን ያሸነፈች ሀገር ሆናለች።
ኖርዌይ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
ሁለቱ ሀገራት አስቀድመው ጥሎ ማለፍ መግባታቸው ይታወቃል።
በጥሎ ማለፉ ፈረንሳንይ ከስዊድን፣ ኖርዌይ ከኮትዲቯር ይገናኛሉ።