ቀጥታ፡

ሕዝቡ የጣለብንን ኃላፊነት እና እምነት በቅንነትና በትጋት በማገልገል እንወጣለን -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ የጣለብንን ኃላፊነትና እምነት በቅንነትና በትጋት በመወጣት ማህበረሰባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ እንሠራለን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የምርጫው ስኬት ሕዝቡ የሚፈልገው ልማት፣ ዴሞክራሲና ዘላቂ ሰላም መሆኑን ማሳየቱንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።


 

በመድረኩ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ እንዲሁም ሌሎች የከተማዋ የስራ ኃላፊዎችና ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ዕውቅና የተሰጣቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥትን ለመመስረትና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ለስኬታማነቱ አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።

በአዲስ አበባ ምርጫው እንዳይሳካ የሚፈልጉ አንዳንድ አካላት ገበያን በማዛባት የዋጋ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ሙከራዎች ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰው፤ በከተማ አስተዳደሩና በባለድርሻ አካላት ትብብር በተወሰዱ እርምጃዎች የተረጋጋ ምህዳር መፈጠሩን አስታውሰዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአንድ ፓርቲ አብላጫ ድምፅ የማግኘት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነም አንስተዋል።

የምርጫው ስኬታማነት ሀገራችን በተረጋጋ ሁኔታ እንዳትመራ፣ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳይቀጥሉ፣ ከሕጋዊና ሰላማዊ አካሄድ ይልቅ በኃይልና በጠልፎ መጣል አካሄድ አሁንም በድህነት ውስጥ እንድንቀጥል የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን ህልም ያከሸፈ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በመገናኛ በዙሃን ጭምር ዘመቻ ከፍተው እኩይ ተልዕኳቸውን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በማንሳት፤ ሕዝቡ በጽናት በመቆምና በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የጠላትን ሴራ በማክሸፍ የሚያኮራ ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።

ሕዝቡ የሚፈልገው ልማት፣ ዴሞክራሲና ዘላቂ ሰላም መሆኑን በተግባር አሳይቷል ያሉት ከንቲባዋ፥ ከሕጋዊ ምርጫ ውጭ ያሉ አካሄዶችን እንደማይቀበል ያሳየው የፀና አቋም ትልቅ ክብር የሚሰጠው ነው ብለዋል።

የተጣለብንን ኃላፊነትና እምነት ከልብ በመቀበል በቅንነትና በትጋት በማገልገል ማህበረሰባችንን እንክሳለን ያሉት ከንቲባዋ፤ በሁሉም መስክ አዳዲስ ስኬቶችን የማስመዝገብ ጉዞ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ በምርጫው የተገኘው ውጤት የጋራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለምርጫው መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት ለሥርዓተ መንግስት ግንባታ አዎንታዊ ድርሻ መወጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ለሁለንተናዊ ብልፅግና በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ስርዓት አስተማማኝ መሰረት የጣለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ናቸው።

ብልፅግና ፓርቲ በአሻጋሪ እሳቤዎቹ ለውጤት መብቃቱንም በመጥቀስ፤ ለፓርቲው በተለያየ መንገድ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም