ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ የአፍሪካ የተስፋና የብልፅግና ተምሳሌት እየሆነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ የአፍሪካ የተስፋና የብልፅግና ተምሳሌት እየሆነች ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ ልማት፣ በከተማ ልማት እና ሌሎችም መስኮች የአፍሪካ የተስፋና የብልፅግና ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላትም ዛሬ ከአራዳ ክፍለ ከተማ አመራሮች ጋር በመሆን በአራት ኪሎ አካባቢ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ የማኖር ሥራ በኢትዮጵያ በተጨባጭ ትላልቅ ውጤቶችን እያስመዘገበ የሚገኝ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት የምክር ቤቱ አባላት ከአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ችግኝ የተከሉበት ቦታ በአሁኑ ወቅት ለምልሞ «ጫካ» መሆን መቻሉን ጠቅሰው፥ ይህም መርሃ ግብሩ በተግባር ውጤት እያሳየ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ የሰውን ልጅ እየፈተኑ ካሉ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛው መሆኑን የጠቀሱት ተጠሪ ሚኒስትሩ፥ ይህ የዓለም አየር ንብረት ለውጥ የመጣው በሰው ልጅ አላስፈላጊ የተፈጥሮ ጣልቃ ገብነት ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍና ለመቀነስ በዓለም መድረኮች ላይ የተለያዩ ስምምነቶች፣ ውይይቶችና ኮንፈረንሶች እየተካሄዱ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን በተግባር የተለየ ታሪክ ለዓለም እየጻፈች ትገኛለች ብለዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በተደረገው ከፍተኛ ሕዝባዊ ንቅናቄ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከልና ተንከባክቦ በማጽደቅ ለተለያዩ ዓላማዎች ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።
ዘንድሮ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተደራጀ መልኩ የራሳቸውን ታሪካዊ ድርሻ ለማበርከት በንቅናቄው እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገሪቱ በምግብ ራስን የመቻል ግብንና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም ከሰባት ዓመታት በፊት የተተከሉ ዘርፈ ብዙ ተክሎች ዛሬ ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም የተነሳ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ አፕልና ሎሚ ያሉ የተለያዩ ምርቶች እንደየአካባቢው የግብርና ሥርዓተ ምህዳር ከፍተኛ ምርት እያስገኙ ነው ያሉት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቮካዶ ከሀገር ፍጆታም ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል አረንጓዴ ዐሻራ ባስገኘው ለውጥ የአበባ እፅዋቶች በመብዛታቸው በሀገሪቱ ለንብ ማነብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና የማር ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል።
በመርሃ ግብሩ ከተፈጥሮ መጎዳት ጋር ተያይዞ የመጣውን በረሃማነትና ድርቅን የመግታትና የመቆጣጠር ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
የአፈር መሸርሸርን ማስቆም የተቻለ ሲሆን፣ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር የውሃ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ የጠፉ ምንጮችና ሐይቆችም መልሰው እያገገሙ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህ የውሃ ሀብት ማደግ ደግሞ በሀገሪቱ የመስኖ ልማት ሥራ እንዲጨምር በማድረጉ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ እጅግ ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በከተማ ልማት እንዲሁም በስንዴ ልማትና በሌሎችም መስኮች ለአፍሪካውያን ጭምር አዲስ የተስፋና የብልጽግና ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።
“ተስፋን እንትከል” የሚለው የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መሪ መልክትም የተቀረጸው ከዚህ በመነሳት መሆኑን ጠቅሰው፥ ተስፋ ያላት ሀገር፣ ተስፋ ያለው ሕዝብና ተስፋ ያለው ትውልድ እየተገነባ ነው ብለዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ለነገ የሚደረግ ትልቅ ኢንቨስትመንትና የነገ ተስፋ መሆኑን በመግለፅ፥ በአሁኑ ወቅት የችግኝ ተከላ ሥራ የሕዝብ የሥራ ባህልና ተቋማዊ አሠራር እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ዜጎች በየቤታቸው፣ በየአካባቢያቸውና በየማሳቸው ጭምር ችግኝ ማፍላትና መትከል መደበኛ ሥራቸው መሆኑን በማንሳት።
የምክር ቤት አባላት የጀመሩትን የችግኝ ተከላ ሥራ ክረምቱን ወደ መረጣቸው ማኅበረሰብ ሲመለሱ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።