ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት አህጉራዊ ኃላፊነቷን በብቃት እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳልጡ ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት አህጉራዊ ኃላፊነቷን በብቃት እየተወጣች መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላቸውን የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንትና የጂኦፖለቲካዊ ትስስር ይበልጥ ለማሳደግ ያለመ "ሂሊ ዲያሎግ-አፍሪካ ኤዲሽን" የምክክር መድረክ ተካሂዷል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በመድረኩ፤ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያሳልጡ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ውጤታማ ስራ እያከናወነች ነው ብለዋል።

በዚህም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በመንገድና በመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳልጥ ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እስከ ታንዛኒያ ድረስ የኤሌክትሪክ መስመር በመዘርጋት የምትሰራው ውጤታማ የልማት ሥራም አህጉራዊ ኃላፊነቷን በብቃት እየተወጣች መሆኗን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063ን ዕውን ለማድረግም አባል ሀገራት የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳልጡ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊና ቀጣናዊ የመሰረተ ልማት ውጤቶችም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያፋጥኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለዲጂታል ኢኮኖሚ የተሰጠው ትኩረትም ንግድና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሃብቶች ጨምሮ ለውጭ አልሚዎች አስቻይ ምኅዳር መፍጠሩን አስረድተዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የስትራቴጂክ ጥናትና ምርምር ማዕከል ኢኮኖሚስትና ተመራማሪ መሐመድ አል አባቢ በበኩላቸው፤ አፍሪካ በሁሉም መስክ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ስትራቴጂክ አጋር ናት ብለዋል።

በዚህም በምግብ ዋስትና፣ በታዳሽ ኃይልና ቁልፍ መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር በመፍጠር እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም