በካፋ ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ126 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በካፋ ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ126 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል
ቦንጋ ፤ ሰኔ 19 /2018 (ኢዜአ)፦ በካፋ ዞን በዘንድሮ የመኸር አዝመራ ከ126 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ የ2018 ዓመተ ምህረት የግብርና ተግባራት አፈጻጸም ግምገማና የ2018/19 የመኸር ግብርና ስራዎች ዕቅድ ንቅናቄ መድረክ አካሄዷል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
ግብርና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማስመዝገብ ወሳኝ ዘርፍ በመሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግና ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተል ያለውን አቅም አስተባብሮ ወደ ስራ በመግባት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በዘንድሮው የመኸር እርሻ 126 ሺህ 491 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን ገልፀዋል።
በዚህም የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በየደረጃው በቁርጠኝነት ይሰራል ያሉት አስተዳዳሪው፣ ለአረንጓዴ አሻራ፣ ለቡና ልማትና ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ልዩ ትኩረት ይሰጣል ነው ያሉት።
የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገረመው ገብሬ በበኩላቸው በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ3 ሚሊዮን 225 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ለዚህም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን 40 በመቶ በማድረስና 30 በመቶ የሚሆነውን መሬት በክላስቴር በማልማት የታቀደውን ያህል ምርት ለማምረት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
የግብዓት እጥረት እንዳይገጥም የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ያነሱት አቶ ገረመው የማይታረስ መሬትን ዜሮ በማድረስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በዘንድሮው የመኸር አዝመራ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ባለፈ ለኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት በመስጠት ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰሩ የገለፁት ደግሞ የጠሎና ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ አትርሴ ሸታቸው እና የሺሾ እንዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሴ ገብረማርያም ናቸው።
በ2017/18 የመኸር አዝመራ ከ123 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡንም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።