በከተማው በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ሆነዋል
ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፡-በወላይታ ሶዶ ከተማ በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን የከተማዋ ከንቲባ እታገኝ ኃይለማርያም ገለጹ።
በከተማው "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ የ2018 ዓ.ም የበጋ ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ እታገኝ ኃይለማርያም እንደገለጹት በከተማዋ በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በዘንድሮ ክርምትም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚከናወኑ ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማከናወን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ግብ ተጥሏል ነው ያሉት።
ለክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሰጠው ልዩ ትኩረት 219 የአቅመ ደካማ ቤቶች የሚገነቡና የሚታደሱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለሥራው ውጤታማት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና ግለሰቦችን በማቀናጀት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳትና በዘላቂነት ለማቋቋም በተለየ ትኩረት ይሰራል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የከተማው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር ዘገየ ጳውሎስ ናቸው።
በዘንድሮ ክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ 40 ሺህ 500 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
የከተማው ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ቡቃቶ በበኩላቸው በክረምት የበጎፍቃድ አገልግሎት ችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ ቤት ግንባታና ዕድሳትን ጨምሮ በ18 ዘርፎች የበጎ ፈቃድ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በተግባሩም 150 ሺህ የሚደርሱ የከተማው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ነው ያመለከቱት።
በዛሬው እለት የቤታቸው ግንባታ ሥራ የተጀመረላቸው አቶ ማሞ ፋራንጆ እና ወይዘሮ አይናለም አሻ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው ቤት በመጎሳቆሉ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ለችግር ሲጋለጡ ቆይተዋል።
ዛሬ ቤታቸው በአዲስ መልክ ግንባታው በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቁመው፣ ድጋፍ ያደረጉላቸውን አካላት አመስግነዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።