ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በምርምር፣በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በማህበረሰብ አገልግሎት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በምርምር፣በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በማህበረሰብ አገልግሎት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
ጂንካ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፡-ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው ባለፈ በምርምር፣በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በማህበረሰብ አገልግሎት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ አገልግሎቶች ያስገነባውን ዘመናዊ ህንፃ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በዚሁ ሁነት ላይ ባደረጉት ንግግር ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው ባለፈ በምርምር፣በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በማህበረሰብ አገልግሎት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው የፕሮጀክቱ መመረቅም ለስራው ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በብቁ የሰው ሃይል እና በተደራጀ ግብአት እራሱን እያጠናከረ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ለላቀ ስኬት መትጋት እንዳለበት ተናግረዋል።
የውስጥ ገቢ አቅሙን በማሳደግና ተቋማዊ አቅሙን በማጠናከር ራስ-ገዝ ለመሆን ጠንክሮ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር ጠንካራ የምርምር ማእከል ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም አፅኖት ሰጥተዋል።
ለዩኒቨርሲቲው ስኬታማ ጉዞ የስራ አመራር ቦርዱ ድጋፍና እገዛውን በማጠናከር የሚቀጥል መሆኑንም አቶ አገኘሁ አረጋግጠዋል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (ዶ/ር )፤ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ፣ብቁ የሰው ሀይል ማፍራትና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን የማበልፀግ ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ አቋሙን ለማጠናከር የካፒታል ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።