ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አዳዲስ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂካዊ የትብብር ፖሊሲዎች የሚፈልቁባት ማዕከል ሆናለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናውና በዓለም ያላት ዲፕሎማሲያዊ ሚና ትብብርን የሚያጠናክሩ አዳዲስ ፖሊሲዎች የሚፈልቁባት ስትራቴጂካዊ መድረኮች ማዕከል እንድትሆን ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ።

የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላቸውን የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንት እና የጂኦፖለቲካዊ ትስስር ይበልጥ ለማሳደግ ያለመው "ሂሊ ዳያሎግ - አፍሪካ ኤዲሽን" የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ረሺድ አብዱላ አልሼኺ እና የተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

የመድረኩ ዓላማ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር፣ በምጣኔ ሀብትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ የጋራ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም ለአፍሪካ አመለካከቶችና ፍላጎቶች በዓለም አቀፍ መድረክ መሪ ሚና ለመጫወት ነው።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ቀጣይነት ባለው ውይይት፣ በጋራ ምርምር እና በእውቀት ልውውጥ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ተቋማዊ አጋርነት መገንባት በአፍሪካና በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ትብብር ለማሳደግ አስፈላጊ ነው።

የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ በአፍሪካም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ግዙፍ አቅም የገነባች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ያስመዘገበችውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እና የኢንቨስትመንት አቅም መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ስልታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከደረሰችበት የቴክኖሎጂ እድገት፣ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት እና ከወደብ ተደራሽነት መስፋፋት ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የበለጠ በጋራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።


 

ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን እምቅ የትብብር አቅምና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በጋራ ጥቅም ላይ ማዋል በሚችሉባቸው ስልታዊ ስምምነቶች ላይ ትኩረት አድርገው እየመከሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የዲፕሎማሲ የሀሳብ አመንጭነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልቶ እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል።

ታዋቂው ኤምሬትስ የስትራቴጂክ ጥናትና ምርምር ማዕከል እውቅና ያለውን የሂሊ ዳያሎግ መድረክ በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት የወሰነው ሀገሪቱ ያላትን ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ፣ የማዕከልነት ሚና እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ መድረኩን እንድታስተናገድ መመረጧ፣ ከተማዋ እያስመዘገበች ያለውን ዕድገትና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን በማዘጋጀት ላለችው ስኬቶች እውቅና የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አዳዲስ የፖሊሲ ሀሳቦች የሚፈልቁባት እና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ዓውደ-ጥናቶች የሚካሄዱባት ስትራቴጂካዊ ስፍራ ሆናለች ነው ያሉት።


 

በኢትዮጵያ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ረሺድ አብዱላ አልሼኺ በበኩላቸው፤ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንትና በጋራ ጥቅሞች ላይ ወደ ተመሰረተ ዘላቂ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት በተለይም በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና እና በንጹህ ኢነርጂ ዘርፎች ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

ኤምሬቶች የአፍሪካን የንግድ እንቅስቃሴ ከቀጣናዊ እና ከዓለም አቀፍ ገበያዎች ጋር ይበልጥ ለማስተሳሰር የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ የልማት ስራዎችን እያከናወነች መሆኗንም ተናግረዋል።

ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ የሚገኘው የኢትዮጵያና የኤምሬቶች ስትራቴጂካዊ አጋርነት ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር እና ሰፊ ዕድልን የመጠቀም ትብብር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም