የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የተለያዩ የብድርና ድጋፍ ስምምነት አዋጆችን አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የተለያዩ የብድርና ድጋፍ ስምምነት አዋጆችን አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረሙ ሶስት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነት አዋጆችን አጸደቀ፡፡
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ በዛሬው እለት ተካሂዷል።
ለምክር ቤቱ ከቀረቡት ስምምነቶች መካከል የመጀመሪያው ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል የአራት መቶ ሰላሳ ሰባት ሚሊዮን አራት መቶ ሺ (437,400,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡
ሁለተኛው የማህበረሰብ ተኮር የመሬት አያያዝ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል የአንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ (145,500,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡
ሶስተኛው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመስኖ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሀምሳ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ (54,600,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡
ምክር ቤቱም እነኚህን የብድርና ድጋፍ ስምምነት አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት፤ የብድርና ድጋፍ ስምምነቶች ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት ተግባራት ምን ያክል ለውጥ እያመጡ እና የህብረተሰቡን ህይወት በተጨባጭ እየቀየሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙን ይበልጥ በማጠናከር፤ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን በመጠንና በጥራት በማሳደግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
የወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ የአርሶና አርብቶ አደሮችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ረብርብ ትልቅ የፋይናንስ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባትና የመስኖ ልማቶችን ለማዘመን እንደሚያግዝም እንዲሁ።