ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ መሪ ያሰኘው አረንጓዴ አሻራ፡ሌላው የኢትዮጵያ የማከናወን አቅም ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ መሪ ያሰኘው አረንጓዴ አሻራ፡ሌላው የኢትዮጵያ የማከናወን አቅም ማሳያ
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያከናወነችው የ"አረንጓዴ ዐሻራ" ንቅናቄ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አገራዊ ግብን ከማሳካት ባለፈ፣ሀገሪቱን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም መሪ እንድትሆን አስችሏታል።
ይህ ታላቅ የተፈጥሮ ጥበቃ ዘመቻ የሀገር ውስጥ የአካባቢ ሚዛንን ከመጠበቅ አልፎ፣ድንበር ተሻጋሪ ዲፕሎማሲያዊ ትስስርን ማጠናከሪያ ስትራቴጂካዊ መሣሪያ እስከመሆን ደርሷል።
ይህ ተሞክሮ የሚያሳየው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ተራ የደን ልማት መርሃ ግብር ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካና ከዚያም ባሻገር ለሚታየው የአየር ንብረት መዛባትና የምድረ በዳነት መስፋፋት ተጨባጭ መፍትሔ ይዛ የቀረበችበት መሆኑን ነው።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ሀገራት ችግኞችን በሕዝብ ንቅናቄ የመትከልና የማጽደቅን ስኬታማ የፖሊሲ አፈጻጸም እንደ ትልቅ ልምድ የቀሰሙበት ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ እና ሩዋንዳን ጨምሮ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ችግኝ ልካለች።
ይህ አረንጓዴ አሻራ የፓን አፍሪካን የአጋርነት መንፈስ አዲስ መገለጫ እና ጉዳዩ የአፍሪካ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን አመላካች ሲሆን አፍሪካውያን በአካባቢ ጥበቃ ዘላቂ ትብብር መፍጠር እንዳለባቸውም የሚያስገነዝብ ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ ያሳየችው ጥረት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም በላይ፣ የአካባቢ ጥበቃን ለቀጣናዊ ሰላምና ትብብር መሠረት ማድረግ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ታላቅ ስኬት ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም በተጀመረው አረንጓዴ አሻራ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
አረንጓዴ አሻራ በአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ከተሰጡ ሀገር በቀል ምላሾች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
ዘንድሮም የተያዘውን የ8 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ ለማሳካት በሚደረገው ብሔራዊ የንቅናቄ ስራ ላይ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።