ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ አፍሪካዊት ተምሳሌት ሀገር ናት -የጎረቤት ሀገራት ፍልሰተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ አፍሪካዊት ተምሳሌት ሀገር ናት -የጎረቤት ሀገራት ፍልሰተኞች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የምታሳየው የእንግዳ ተቀባይነት አያያዝ አፍሪካዊት ተምሳሌት ሀገር እንደሚያሰኛት የጎረቤት ሀገራት ፍልሰተኞች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበል ተገቢውን መስተንግዶ እያደረገች ትገኛለች።
በኢትዮጵያ ለሚገኙ ፍልሰተኞችም የዲጂታል መታወቂያ በማዘጋጀት ጭምር ከተቀባዩ ማህበሰረሰብ ጋር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክሩበት ምኅዳር ተፈጥሯል።
በቅርቡም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያዎች ያላቸውን ሕይወት ከሀገሪቱ ብሔራዊ ሥርዓቶች ጋር ማስተሳሰርን ማዕከል ያደረገ የማካተት ፍኖተ ካርታ በይፋ አስጀምሯል።
አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በእንግዳ ተቀባይነት ባህል ከመቀበል ባሻገር የልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አስደናቂ ስራ እየሰራች ነው።
ከኮንጎ የመጣው ወጣት ጆሴፍ ንዲኩሙኪዛ፤ ከአሥር ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ እየኖረ እንደሚገኝ ገልጿል።
የኢትዮጵያ የእንግዳ ተቀባይነት ባህልም ከተቀባዩ ማህበረሰብ ጋር ጭምር በሚያስተሳስር የልማት መርሃ ግብር ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ አስደናቂ ተግባር የታጀበ መሆኑን ተናግሯል።
የአህጉሪቷ አባል ሀገራትም ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የምታሳየው የእንግዳ ተቀባይነት አያያዝ ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝቧል።
ቡሩንዲያዊቷ ወጣት ሶሃንጌ ንዳይራጊሴ ማባንጋ በበኩሏ፤ ኢትዮጵያውያን ሰው አክባሪና በማንኛውም ሰዓትና ሁኔታ ድጋፍ የሚሰጡ ቀና ህዝቦች ናቸው ብላለች።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ለስደተኞች ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ዕድሎችን በማመቻቸት ከፍተኛ ድጋፍና እገዛ እያደረጉላቸው እንደሚገኝ አስረድታለች።
ኢትዮጵያ እንደሀገሬ ተሰምቶኝ የምኖርባት ሁለተኛ ሀገሬ ናት ያለችው ደግሞ ኬንያዊቷ ወጣት ሃና ፓትሪክ ናት።
የኢትዮጵያዊያን ደግነት ከሀገሯ ጉርብትና ጋር ተዳምሮ ደስተኛ ህይወት እንድትቀጥል ማስቻሉን ገልጻለች።