ብልፅግና ፓርቲ አካታች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እውን እያደረገ ነው -ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ አካታች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እውን እያደረገ ነው -ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ አግላይ እሳቤዎችን በማስወገድ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አካታች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እውን እያደረገ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በዚሁ መድረክ ላይ የብልፅግና ፓርቲ የሱማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ፣ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ፓርቲው አግላይ እሳቤዎችን በማስወገድ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አካታች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እውን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ በስኬት እየተራመደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፓርቲውን እሳቤ ወደ ማኅበረሰቡ በማስረጽ ረገድ አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት ያለመውን ይህንን መድረክ ላዘጋጁት የሱማሌ ክልል አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
ለዘመናት ከመሀል ፖለቲካ ተገልሎና ከአገሪቷ ኢኮኖሚ ፍትሐዊ ተጠቃሚ ሳይሆን የኖረው የሱማሌ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በመሀል ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማደጉን ተናግረዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በክልሉ የመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ትልቅ መነቃቃት መፈጠሩን ያነሱት ኃላፊው፤ የሱማሌ ክልል ሕዝብ ለዘመናት ሲናፍቃቸው የቆዩትን እንደ ጤና፣ መንገድና ትምህርት የመሳሰሉ መሠረታዊ የልማት አውታሮች በስፋትና በጥራት ተጠቃሚ መሆን መቻሉን አብራርተዋል።
ይህ ለቀጣዮቹ ቀናት የሚቆየው የጅግጅጋው መድረክ፣ የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በጥልቀት በመገምገም፣ በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርግ ታውቋል።