ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባሻገር ለምግብ ዋስትና ትልቅ አቅም እየሆነ ነው

ሠመራ፤ ሰኔ 19/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባሻገር ለምግብ ዋስትና ትልቅ አቅም መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በገቢ ራሱ ዞን አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ አስጀምረዋል።


 

በዚሁ ሁነት ላይ እንደተናገሩት እንደ ሀገር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

በአፋር ክልልም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባሻገር ለምግብ ዋስትና መሰረት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አንስተው ዘንድሮም ልማቱ በተጠናከረ መልኩ ይከናወናል ብለዋል።

በዚህም ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አንስተው፤ 60 ከመቶ የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ለእቅዱ መሳካት የክልሉ ህዝብ አሻራውን በማኖር በልማቱ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።


 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ያሲን ዓሊ በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 41 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።

በዘንድሮ ዓመትም በ6 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም