ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጠቀሜታ ከአገልግሎትም በላይ የሚሻገር ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ

በንሳ ዳዬ፤ ሰኔ19/2018(ኢዜአ) ፦ በየዓመቱ የሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለዜጎች የሚሰጠው ጥቅም ከአገልግሎትም በላይ እንደሆነ የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች አስረክበዋል።


 

በዚህ ወቅትም ርዕሰ-መስተዳድሩ እንዳሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን እለታዊና ዘላቂ ችግሮች ከመፍታት ባለፈ እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህልን የሚያጎለብት የጋራ ማንነትንም የሚገነባ ነው።


 

በሲዳማ ክልል የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊ ችግሮች እየፈቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ተግባሩን ለማስቀጠልም ቅንጅታዊ ሥራዎች እንደሚጠናክሩ የገለጹት አቶ ደስታ፣ ዛሬ በዳዬ ከተማ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የተገነባው ቤትም የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል።


 

ዛሬ የመኖሪያ ቤት ቁልፍ ከተረከቡ የበንሳ ዳዬ ከተማ አቅመ ደካሞች መካከል የ90 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ወይዘሮ ሙላቷ ይማም እንዳሉት ቤቱን በማግኘታቸው ዳግም የተወለዱ ያህል መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በዕድሜ መግፋት ምክንያት መስራት እንደማይችሉና የሚደግፋቸውም እንደሌለ ጠቅሰው ለተደረገላቸው ድጋፍ የክልሉን መንግስት አመስግነዋል።

የተሰራላቸው መኖሪያ ቤት የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥና ለሱቅ ጭምር የሚከራይ ክፍል የተዘጋጀለት በመሆኑ ቀጣይ ህይወታቸውን ለመምራት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

ከክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በበጋ ወራት በ13 ዘርፎች ከ654 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎሩ ከ354 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም