ቀጥታ፡

ሰው ተኮር ልማት - የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ስኬታማ ተግባር

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሰው ተኮር ልማት ባከናወነቻቸው ተግባራት የዜጎችን ኑሮ ያሻሻሉና ሰብዓዊ ክብርን ያጎናጸፉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን አስመዝግባለች

የሰው ተኮር ልማት ጽንሰ ሃሳብ የሰው ልጅ ጤናማ፣ ክብር ያለው ኑሮን እንዲጎናጸፍ የማድረግ ዕድልና አቅሞችን የማስፋት ሂደት ነው። ይህ ጽንሰ ሃሳብ የአንድ ሀገር ዕድገት በኢኮኖሚ ወይም በገቢ መጠን ብቻ የሚለካ እንዳልሆነ ያሳያል። ይልቁንም የሰዎች የኑሮ ጥራትና ዕድሎች መስፋት ዋናው መለኪያ መሆኑንም ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ሰው ተኮር ልማት- ሰብዓዊ ክብርን የማጎናጸፍ መሠረት

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በእሳቤም በገቢርም ሰው ተኮርነትን ማዕከል ያደረገ አዲስ የልማት አቅጣጫ በመተለም ወደ ተግባር ተገብቷል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከግቢ እስከ ሀገር እየተተገበሩ ካሉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች አንዱ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቧሬ አካባቢ የአቅመ ደካማ ዜጎችን ደሳሳ ቤቶች በማደስ ወደ ዘመናዊ መኖሪያ መንደርነት ቀይረዋል። ይህ እሳቤና ተግባር  አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ ባህል እየሆነ መጥቷል። የመንግሥት እቅድ፣ የህብረተሰብ የገንዘብ፣ የእውቀትና የጉልበት ተሳትፎ ተደምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነፍሶችን እፎይታ አስገኝቷል። 

በየዓመቱ የሚከናወኑ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ አስችሏል። በዚህም ዜጎች በተሻለ ሁኔታ ህይወታቸውን የሚመሩበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በርካታ ጎስቋላ መንደሮችን በማደስ፣ የምገባ ማዕከላትን በማስፋፋት፣ የልማት ተነሺ የጋራ መኖሪያ መንደሮችና ሌሎችም የልማት ፕሮጀክቶች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከቱ ይገኛል።

ቀደም ሲል በጎስቋላ ቤት ውስጥ ብርድና ጸሐይ፣ ዝናብና ንፋስ እየተፈራራቁባቸው በተመሰቃቀለ መንገድ ህይወትን ይኖሩ የነበሩ አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያንና የሀገር ባለውለታዎች ዛሬ ላይ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያና ማረፊያ ቤት ተገንብቶላቸዋል። ከቁዘማና ትካዜ ወጥተው ሀሴትን ተጎናጽፈዋል። ሰብዓዊ ክብርንም ተቀዳጅተዋል።

የለውጡ መንግሥት ባህል እንዲሆን እያደረገ ያለው ሌላኛው ሰው ተኮር ተግባር ማዕድ ማጋራት፣ የምገባ ማዕከላትን ማስፋፋትና የትምህርት ቤት ምገባ ነው። 

የማዕድ ማጋራት መርኃ ግብር ህብረተሰቡ ካለው ላይ አካፍሎ ለአቅመ ደካሞች በመለገስ አብሮነቱን የሚያረጋግጥበት፣ አቅመ ደካሞች በዓላትን በደስታ የሚያሳልፉበትን አውድ ፈጥሯል። የምገባ ማዕከላት በየአካባቢው  እየተስፋፉ ሲሆን ይህም በቀን አንድ ጊዜ  መመገብ የማይችሉ ዜጎች ምግብ የሚያገኙበትን ዕድል ያመቻቸ ነው። ከዚህ በላይ ሰው ተኮርነት ሊኖር አይችልም።

የትምህርት ቤት ምገባ መርኃ ግብር በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በስፋት ተግባራዊ ሆኗል። ይህም ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን በአግባቡ የሚከታተሉበትን አስቻይ ምህዳር ፈጥሯል። ይህም ለብዙ አቅመ ደካማ ዜጎችና ለልጆቻቸው እፎይታን ሰጥቷል። 

የአዲስ አበባ የሰው ተኮር ልማት አብነቶች!

በአዲስ አበባ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በአጭር ጊዜ የተገነቡ ሰው ተኮር የልማት ውጤቶች የከተማ ልማትና የህብረተሰቡን ኑሮ በማሻሻል በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።  መዲናዋ ለአቅመ ደካማ ዜጎች የኑሮ ሁኔታን በማሻሻል በአብነት የምትጠቀስ ከተማ ሆናለች። ከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡንና ባለሀብቶችን በማስተባበር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደሳሳ ቤቶችን አድሷል። በርካታ የምገባ ማዕከላትን በመክፈት ምግብ ለማያገኙ ዜጎች ደርሷል። የትምህርት ቤት ምገባን ተቋማዊ በማድረግ በአርዓያነት የሚጠቀስ ሥራ አከናውኗል። ከዚህም ባለፈ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሰው ተኮርነትን ማዕከል አድርገው እንዲገነቡ የማድረግ ባህልን ፈጥሯል። በዚህም የሚጨበጥና ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነትን አረጋግጧል።

ሌላኛው የሰው ተኮር ልማት ትሩፋት እያንዳንዱ የልማት ፕሮጀክት አካታችነትን ያረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ለአብነትም የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት የዜጎችን አኗኗር በማዘመን፣ ገጠርና ከተማን ደረጃውን ወደ ጠበቀ የዕድገት ምዕራፍ በማሸጋገር፣ የተሰናሰለ ልማትን በማምጣት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ይገኛል።

የአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማን ገፅታ ብቻ አይደለም የቀየረው፤ በስጋትና በሰቀቀን ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎችን ነፍስ የታደጉ፣ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካማ ዜጎችና ለታዳጊዎችም ምቹ ከባቢን እውን ያደረገ ነው። የእነዚህ ፕሮጀክቶች ዋና እሴት የተጋላጭ ዜጎችን ክብር በመጠበቅ፣ የኑሮ ጥራታቸውን በማሻሻል  ማንም ወደኋላ የሚቀር የለም የሚል የአካታች ልማት መርህን  በተግባር ማረጋገጠም ነው።

የኢትዮጵያ ዕድገት ከዜጎቿ ፍላጎት ጋር የተሰናሰለ ነው!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት፥ ሰው ተኮር ልማትንና ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን በመንግስት በጀት ብቻ ማረጋገጥ አይቻልም፤ የሰው ጉልበት፣ እውቀትና ሃብት ከመንግስት እቅድ ጋር ተደምሮ ሲተገበር በርካታ ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በሰው ተኮር የልማት አቅጣጫዋ፣ የመንግሥትን እቅድና የህብረተሰብን ተሳትፎ በማስተባበር በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዘርፎች በሠራችው ሥራ ለትውልድ የሚበጁ ውጤቶች እየተገኙ  ነው።

ለአብነትም ባለፉት ዓመታት ከ35 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። በርካታ የጤና ተቋማትም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር ተገንብተው ተደራሽ የጤና ሥርዓትን ለማስፋፋት አቅም ፈጥረዋል።

ማህበራዊ የጤና መድህን ሥርዓትን በማስፋፋት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች በቂ ህክምና እንዲያገኙ አድርጓል።

የኢትዮጵያ እውነተኛ ዕድገት የሚለካው በሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎቿን ፍላጎት በመረዳት ሕይወታቸውን በሚያሻሽሉ አገልግሎቶችና ዕድሎች ነው።

የልማት ፖሊሲዎች የሕዝብን ፍላጎት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሲያስቀድሙ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማህበራዊ ፍትሕና ዘላቂ ልማት ጋር ተጣጥሞ ይጓዛል።

ስለዚህ የኢትዮጵያ የወደፊት ስኬት መሠረቱ የእያንዳንዱን ዜጋ ፍላጎት በማክበር፣ እኩል ዕድልን በማስፋትና የልማት ፍሬዎች ለሁሉም እንዲዳረሱ በማድረግ ይጠናከራል።

በአዲስ አበባና በመላው ሀገሪቱ በመንግሥትና በዜጎች ተሳትፎ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ከዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጋር ተሰናስሎ የሚጓዝ መሆኑን ያለፉት የለውጥ ዓመታት ስኬቶች አብነቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም