የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን በላቀ የአመራር ጥበብ ለመፈፀም በትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን በላቀ የአመራር ጥበብ ለመፈፀም በትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ አረጋ ከበደ
ባሕር ዳር፤ ሰኔ 19/2018(ኢዜአ)፡- በተቋማት እየተካሄደ የሚገኘውን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በላቀ የአመራር ጥበብ በመፈፀም የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለፁ።
በአማራ ክልል በመጀመሪያው ዙር ወደ መንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም የሚገቡ ተቋማትን የቅድመ ዝግጅት ሁኔታ በተመለከተ በባሕር ዳር ከተማ እየተገመገመ ነው።
ርእሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ መንግስት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በመቅረጽ የክልሉ ህዝብ የሚያነሳውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ነው፡፡
በዚህም ለህዝቡ ፈጣን፣ ፍትሃዊና እርካታን የፈጠረ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥም በከተሞች መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግና በተቋማት የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርምን በመተግበር ውጤታማ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የሪፎርሙ ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሪፎርሙ የተቀናጀ መዋቅር፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርና ቁርጠኛ አመራርን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሪፎርሙን በክልል ደረጃ በተሟላ መልኩ በመተግበር ወደ ታች ለማውረድ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።
የዛሬው መድረክ ዋና ዓላማም ቀድመው ሪፎርሙን ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማት አተገባበር ያለበትን ሁኔታ በመገምገም በቀጣይ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያለመ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማርያም እንደገለጹት፤ ባለፉት ሶስት ወራት በስምንት ተቋማት የተጀመረውን የሪፎርም ትግበራን ለማስፋት እየተሰራ ነው።
ተቋማቱ በዝግጅት ምእራፍ ስትራቴጂ በመቅረጽ፣ ማስፈጸሚያ መመሪያ በማዘጋጀትና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት መስክ ያከናወኑት ተግባር አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ከሀምሌ ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሪፎርም ትግበራው ለሚገቡ ተጨማሪ ዘጠኝ ተቋማት ልምድና ተሞክሮ ለማስተላለፍ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
በመጀመሪያው ምእራፍ የሪፎርም ትግበራ ግብርና ፣ ጤና ፣ ትምህርት፣ ስራና ክህሎት፣ ሲቪል ሰርቪስ ፣ ገንዘብ ፣ ገቢዎችና ፕላን ልማት ቢሮዎች መካተታቸው የሚታወስ ነው።