ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተለዩት አጀንዳዎች የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት ያማከሉ ናችው - የሀገር ሽማግሌዎች

አዳማ፣ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ):- ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተለዩት አጀንዳዎች የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት ያማከሉ መሆናቸውን የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባካተተ መልኩ ሲከናወን ቆይቶ በብሔራዊ ደረጃ የሚካሄድ ጉባኤ ላይ ደርሷል።

የኮሚሽኑ አጀንዳ ማሰባሰብና የማደራጀት ተግባር በመጠናቀቁም ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፤ ሐምሌ 08/2018 ዓ/ም በተለዩ ስምንት የመወያያ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተለዩት አጀንዳዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በግልጽ የመነጩ በመሆናቸው የሁሉንም ወገን ፍላጎት ያማከሉ ናቸው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ፈይሳ መገርሳ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባዘጋጀው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ በንቃት መሳተፋቸውን አስታውሰዋል። 

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ምሁራን፣ ሴቶች፣ መምህራን፣ ፖለቲከኞችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የአንጀንዳ ማሳበሰብ ሂደቱ ላይ እንደመቆየታቸው ለብሔራዊ ጉባኤው የተለዩ አጀንዳዎች ወካይ እና ለችግሮቻችን መፍትሄ ለመሻት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

ሀገራዊ ጉባኤው እንዲሳካም የሚጠበቅባቸውን በመወጣቱ ረገድ እያከናወኑ ያሉትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ጥላሁን ራጎ በበኩላቸው፣ በምክክር ሒደቱ ተሳትፈው በሕዝብ ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን አስታውሰዋል።

ለብሔራዊ ጉባኤው የተለዩት አጀንዳዎች የሀገሪቱን ችግር ይፈታሉ የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው "አጀንዳዎቹ አስፈላጊና ከሕዝቡ የመነጩ በመሆናቸው ትክክለኛና ተገቢ ናቸው፤ እኛም ለስኬቱ የበኩላችንን ድርሻ እናበረክታለን" ብለዋል።

ለዚህም በተመረጡት አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሮ በመግባባት ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በምክክሩ የተወከሉ አካላት ተወያይተው ያጸደቁትን ሐሳብ የመቀበል ግዴታ አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም