ቀጥታ፡

ማዕድን ዘርፍ- በሀገራዊ ለውጡ ያንሰራራው የኢትዮጵያ አቅም

በሙሴ መለሰ

የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ በአገር በቀል የኢኮኖሚና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ታግዞ፣ ባለፉት ዓመታት የታዩበትን የአሰራርና መዋቅራዊ ችግሮች በመቀረፍ ከፍተኛ የመነቃቃት ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንደገለጹት፣ ማዕድን በብዝኃ ዘርፍ የልማት ምልከታችን ውስጥ እና በአገሪቱ የሰላሳ ዓመታት የልማት ዕቅድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ቁልፍ ዘርፍ ሆኖ ይቀጥላል።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው የላቀ ትኩረትና ባከናወናቸው የማስተዋወቅ ሥራዎች፣ የማዕድን ልማት በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ውስጥ የማዕድን ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያበረከተው አስተዋጽኦ ከዜሮ ነጥብ ስምንት በመቶ በታች የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን አስገራሚ መዋቅራዊ ሽግግር እየተመዘገበ ይገኛል።

በቅርብ የወጡ የቁጥር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ብቻ ዘርፉ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ በማስመዝገብ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ያለውን ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል። 

ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ92 በመቶ የገቢ ዕድገትና የ27 በመቶ የምርት መጠን ብልጫ ማሳየቱን ያረጋግጣል። ምርቶቹ በከፍተኛ ደረጃ የሚላኩትም ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ አሜሪካ፣ ጀርመን እና ቻይና የመሳሰሉ ግዙፍ የዓለም ገበያዎች ነው።

በዚህ ታሪካዊ ስኬት ውስጥ የወርቅ ምርት የወጪ ንግድ ዘርፉ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚመመዘገብ ማዕድን አይነት ነው።

የወርቅ ወጪ ንግድ በያዝነው ዓመት ከአምስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ይህም እንደ ከፍተኛ እምርታ ነው ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት ብቻ 22 ነጥብ 5 ቶን ወርቅ ለውጭ ገበያ የቀረበ ሲሆን፣ እስከ ዓመቱ ማብቂያ ድረስ መጠኑ 32 ቶን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት የወርቅ ምርቱ 95 በመቶ የሚሆነው በባህላዊ አምራቾች ዘዴ የሚመረት ቢሆንም፣ ይህንን አሠራር ይበልጥ ዘመናዊና ውጤታማ ለማድረግ መንግሥት አነስተኛ የወርቅ ማጣሪያና ማቅለጫ ፋብሪካዎችን ለመገንባት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ከውጭ የሚገቡ ስትራቴጂክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። በዚህም መሠረት በየዓመቱ ለከሰል ምርት ግዢ ይወጣ የነበረውን 300 ሚሊዮን ዶላር ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የተቻለ ሲሆን፣ የሲሚንቶ ምርትም ባለፉት ስምንት ዓመታት ከነበረበት ስምንት ሚሊዮን ቶን አሁን ላይ በዓመት ወደ 14 ሚሊዮን ቶን ምርቱ እንዲያድግ ተደርጓል።

በተመሳሳይ መልኩ አገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባውን የተፈጥሮ ጋዝ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሀገር ውስጥ የማምረት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ይህም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጉባ ብስራቶች መካከል አንዱ ነው።

ይህንን ተከትሎም በአዲስ አበባ-ጂቡቲ ኮሪደር ላይ ሦስት የጋዝ መሙያ ማደያዎች የተገነቡ ሲሆን፣ ከ1 ሺህ 500 በላይ የከተማ አውቶቡሶችን ከናፍጣ ነዳጅ ወደ ጋዝ የመቀየር  የሽግግር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

 

በሌላ በኩል የብሔራዊ ኢኮኖሚው ምሰሶ የሆነውን የግብርና ዘርፍና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማጠናከር ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል።

ለ34 ሚሊዮን ያህል አርሶ አደሮች ፍላጎት ማሟያ በየዓመቱ ለማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማስቀረት፣ መንግሥት የማዳበሪያ ፋብሪካ በሚቀጥሉት 29 እስከ 30  ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ እየተሰራ ይገኛል።

ይህም ሙሉ በሙሉ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የሚሸፍን ይሆናል። እንዲሁም በየዓመቱ የብረት ምርትን ከውጪ ለማስገባት የሚወጣውን አንድ ቢሊዮን ዶላር በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል ግዙፍ የፋብሪካ ግንባታ ስምምነት ተፈርሞ ወደ ተግባር ተገብቷል።

እንደሚታወቀው የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ የፕሮጀክቶች መጀመር ብቻ ሳይሆን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅንም  ቀድሞ ታሳቢ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ በቀደመው አሰራር የስምንት ሰዓት እለታዊ ስምሪት ሳይሆን 24 ሰዓታትን በመትጋት ማከናወን የሰርክ ተግባር ነው።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በሀገር ውስጥ እና በወጪ ገበያ ምርት መጠን ላይ ከፍተኛ እድገት እየተመዘገበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በማዕድን ዘርፉ ውስጥ ተሰማርተዋል።

ይህም ከለውጡ በፊት ከነበረውና ከ100 ሚሊዮን ዶላር የማይበልጡ አነስተኛ ኢንቨስትመንቶች የነበሩበትን አሳሳቢ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ የለወጠ ስኬት ነው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በዓለም ላይ ካሉ ያልተነኩ ግዙፍ የፖታሽ ክምችቶች መካከል አንዱ የሚገኝበትን የአፋር ክልል የማልማት ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

ከዚህ ባለፈም ባለፉት 30 ዓመታት ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምርበት እንዲሁ ይላክ የነበረውን የታንታለም ማዕድን፣ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ መንግስት ከአሜሪካ ኩባንያ ጋር ድርድር ላይ ይገኛል።

ከወርቅ በተጨማሪ ለዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂና የባትሪ ምርት ወሳኝ የሆኑትን ሊቲየም፣ ኮባልትና ኒኬል የመሳሰሉ ማዕድናትን በስፋት ለማምረት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ይበልጥ ሳቢና ፍትሐዊ ለማድረግ የአሰራር ማሻሻያዎች ተተግብረዋል። የማዕድን ፍለጋ እና ምርት ፈቃድ አሰጣጥን ግልጽ ለማድረግ አሠራሩ ቅድሚያ የመጣን ቅድሚያ ማስተናገድ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ተደርጓል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍም የወጪ ንግድ ኮንትራት ምዝገባ እና የመላኪያ ፈቃድ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ኦንላይን ሥርዓት የተሸጋገሩ ሲሆን፣ አዲስ ፈቃድ ለማውጣት ወይም ለማደስ የኤሌክትሮኒክስ የንግድ ሥርዓት ድረ-ገጽ እና የማዕድን ካዳስተር ሲስተምም ተዘርግቷል።

በማዕድን ግብይት አዋጅ መሠረት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የማዕድን ላኪነት፣ የሀገር ውስጥ ንግድ፣ የማጣራትና ማቅለጥ እንዲሁም የአቅራቢነትና ዕደ-ጥበብ ፈቃዶች በግልጽና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ እንዲሰጡ ተደርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም በማዕድን ማምረት ሥራዎች የሚገኘው ገቢ የተወሰነ ክፍል ማዕድኑ በሚወጣበት አካባቢ ለሚገኘው ማህበረሰብ ልማት እንዲውል በሕግ ተደንግጎ ወደ ሥራ መተርጎሙ የሕዝብን ተጠቃሚነትም አረጋግጧል።

መንግሥት የኮንትሮባንድ ቁጥጥርን በከፍተኛ ደረጃ በማጥበቅና ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር፣ ምርቶች በይፋዊ የገበያ ሰንሰለት ብቻ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ፈተናዎቹን በቁርጠኝነት እየመከተ ይገኛል።

የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሃና ብርሃኑ ኢትዮጵያ ታከናውናለች በተሰኘው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ እንደገለጹት፣ የመንግሥት ስልታዊ እቅድ እ.ኤ.አ. በ2030 የማዕድን ወጪ ንግድ ገቢን ከማዕድን ዘርፍ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ ነው።

ይህ ታላቅ ራዕይ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስት ቀዳሚ የማዕድን አምራች ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ያለመም ነው።

መንግስት በማዕድን ዘርፍ ያለውን ይህንን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ወደ ላቀ ብልፅግና ለመቀየር በዘርፉ ለሚሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ማበረታቻ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም