አገልግሎቱ በዲጂታል የታገዘ የትራፊክ አደጋ መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ በዲጂታል የታገዘ የትራፊክ አደጋ መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስረከበ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ የትራፊክ አደጋ መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስረክቧል፡፡
የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት፤ በመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመቀነስ በዘርፉ የተቀመጡ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችለውን የግማሽ ዘመን ስትራቴጂ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ ተቋሙ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያለማው የቆየውን በዲጂታል የታገዘ የትራፊክ አደጋ መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስረክቧል።
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ እንደገለጹት፤ አዲሱ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ በዲጂታል የታገዘና ወጥነት ያለው የመረጃ አያያዝ እንዲኖራት ያደርጋል።
ሥርዓቱ በትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ላይ ታማኝነትንና ወጥነትን የሚያሰፍን በመሆኑ፣ በሐሰተኛ መረጃዎች ላይ ተመስርተው በአገሪቱ ላይ የሚወጡ ሪፖርቶችን በተጠናከረና ትክክለኛ መረጃ ለመከላከል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱን ዛሬ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ማስረከባቸውን ጠቅሰው በቀጣይ በሂደቱ ላይ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል፡፡
ሥርዓቱ ከሙከራ እስከ ትግበራ ድረስ ሁለት ዓመታት የፈጀ ሲሆን፣ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም የሥርዓቱ አጠቃቀም ላይ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ጥናቶች መደረጋቸውንና በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በባህር ዳር እንዲሁም በድሬዳዋ ከተሞች ላይ በተደረገው የሙከራ ትግበራ ውጤታማ መሆኑ በመረጋገጡ አሁን ላይ በሁሉም ክልል ከተሞች ተግባራዊ እንዲሆን መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፤ ይህ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን የማዘመን ሂደት አገሪቱ በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የጀመረችው ጉዞ አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ ወቅታዊ፣ አስተማማኝና ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ማግኘቱ የትራፊክ አደጋን ከመከላከል አኳያ ሥራውን በእጅጉ የሚያቀልና የመረጃ አያያዙን የሚያዘምን መሆኑን ጠቅሰዋል።
አዲሱ ሥርዓት በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ጠቅሰው አገራዊ ፖሊሲዎችንና ውሳኔዎችን በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለማውጣት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አደጋዎችን ከመመዝገብ ባለፈ፣ የአደጋውን መንስኤዎች በትክክል መዝግቦ መፍትሄ ለመፈለግ ዕድል እንደሚሰጥ ጠቁመው በሐሰት የሚወጡ መረጃዎችን በተጨባጭ መረጃ በመከላከል፣ ለቱሪዝም እና ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡
የሰለጠነ የሰው ኃይልና ወደ አንድ የጋራ ቋት የሚገባ የመረጃ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል፡፡
አገሪቱ የራሷ የሆነ ብሔራዊ የመረጃ ቋት እንዲኖራት ያደረገ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህንን ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በፍጥነት ወደ ሥራ የማስገባትና የመተግበር ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።