የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳዎች ለሀገራዊ መግባባት መሰረት ይጥላሉ - የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳዎች ለሀገራዊ መግባባት መሰረት ይጥላሉ - የሀገር ሽማግሌዎች
ወልቂጤ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተለዩ አጀንዳዎች ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የጉራጌ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
የጉራጌ የጆካ የሃገር ሽማግሌዎች ሰብሳቢ አጋዝ በለጠ ወልዴ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን ለመለየት የሄደበት ርቀት የሚደነቅ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራት ህዝብን ያሳተፈ እንደነበር አስታውሰው፣ በየደረጃው ሲካሄዱ በነበሩ መድረኮች ህዝቡ ያሉትን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማቅረቡን አስታውሰዋል።
የሃገር ሽማግሌዎችም በምክክር ሂደቱ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም ለሀገራዊ መግባባት የሚሰሩ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በኮሚሽኑ የቀረቡ አጀንዳዎችን ከራስ እና ከአካባቢያዊ ጥቅም በተሻገረ ሁኔታ በመመልከት ችግሮችን በሰከነ መንገድ በመምከር፣ በመወያየት በመግባባት ለሀገር ጥቅም መስራት ይገባል ብለዋል።
አቶ ጠንክር ቢረጋ፤ በሐምሌ ወር ለሚካሄደው ዋናው ሐገራዊ ምክክር ጉባኤ የተለዩት አጀንዳዎች ሳያግባቡ በቆዩ ጉዳዮች ላይ በግልጽ በመነጋገር ለልጆቻችን ታላቅ ሃገር ለማስተላለፍ ያስችለናል ብለዋል።
ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ለችግሮች በጋራ መፍትሔ ማበጀት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የምክክርና የእርቅ ባህልን በማጠናከር በተለዩት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ መግባባት ላይ እንዲደረስ ለምክክሩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የተናገሩት ሌላኛው የሃገር ሽማግሌ ደግሞ ሃይሌ ታቅንዳ ናቸው፡፡
ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በየአካባቢው በዜጎች የተነሱ አጃንዳዎችን አደራጅቶና ወስኖ ማቅረቡ በትኩረቶቹ ላይ ተነጋግሮ መግባባት ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸው፣ ለምክክሩ ስኬታማነት ተሳትፎዋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዳስታወቀው የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል።