በአፍሪካና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድጉ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድጉ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድጉ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላቸውን የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንት እና የጂኦፖለቲካዊ ትስስር ይበልጥ ለማሳደግ ያለመው "ሂሊ ዲያሎግ - አፍሪካ ኤዲሽን" የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ረሺድ አብዱላ አልሼኺ እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
የመድረኩም ዓላማ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር፣ በምጣኔ ሀብትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ የጋራ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም ለአፍሪካ አመለካከቶችና ፍላጎቶች በዓለም አቀፍ መድረክ መሪ ሚና ለመጫወት ያለመ ነው።
መድረኩ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ እና ስትራቴጂካዊ የጥናትና ምርምር ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ቀጣይነት ባለው ውይይት፣ በጋራ ምርምር እና በእውቀት ልውውጥ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ተቋማዊ አጋርነት መገንባት በአፍሪካና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ትብብር ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቁመው፤ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መስተጋብሮችን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ረሺድ አብዱላ አልሼኺ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ ለማሳለጥ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
በወደብ ልማት፣ በኢነርጂ እና በሌሎችም ዘርፈ ብዙ መስኮች ከአፍሪካ ጋር በትብብር እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።