የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እያበረከተ ነው
ድሬደዋ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እያበረከተ መሆኑን የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በድሬደዋ አስተዳደር ቢሻን በሔ ገጠር ቀበሌ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በቢሻን በሔ ቀበሌ ችግኞችን በመትከል አስጀምረዋል።
ከንቲባ ከድር በወቅቱ፤ በአስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በተከናወኑት ተግባራት የጎርፍ ስጋትን ማስቀረትና የግብርና ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ህብረተሰቡ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገርና የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
ውጤቶቹን ለማዝለቅም በዘንድሮው ክረምት ችግኞች የመትከልና የመንከባከብ ስራ በንቅናቄ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ተግባሩም ለድሬደዋ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ህብረተሰቡ ባህሉ አድርጎ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ስኬታማ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉት 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች የአስተዳደሩን የደን ሽፋን ከ18 በመቶ ወደ 36 በመቶ ከፍ ማድረጉን አንስተዋል።
እነዚህ ለደንና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች የአካባቢውን ስነምህዳር በመቀየርና ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አስችለዋል ብለዋል።
ዘንድሮ ከሚተከሉት 5 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከነዚህም ውስጥ 1ሺህ 200 ሄክታር መሬት በብርትኳንና ፓፓያ በክላስተር የሚለማ መሆኑን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ አብዲ ሙክታር እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የቀበሌው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።