በክልሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ዱራሜ ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የዱራሜ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ የመንግስት አገልግሎትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአንድ ቋት የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት የማህበረሰቡን ጊዜና ጉልበት ከመቆጠብ በተጨማሪ ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድ በጎ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በክልሉ በሚገኙ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በዱራሜ ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው 6ኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው፤ የመንግስት አገልግሎትን በማዘመን ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ የማድረግ ስራ በልዩ ትኩረት እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎቱን በሌሎች መዋቅሮች በማስፋት የማህበረሰቡን እርካታ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የዱራሜ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ነፃነት አፌቦ፤ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል በመንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ይስተዋል የነበረን የአሰራር ችግር ይቀርፋል የሚል እምነት እንዳላቸው አመላክተዋል።በማእከሉ ስራ መጀመር መደሰታቸውንም ገልጸዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ አገልግሎቶችን በአንድ ቋት በመሰብሰብ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ እንግልትን ያስቀራል ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ በየነ አርፊጮ ናቸው።
በስነ ስርአቱ ላይ የክልል ፣ የዞንና የዱራሜ ከተማ ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።