ቀጥታ፡

ለምክክር የቀረቡ አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው

ቦንጋ ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ለምክክር የቀረቡ አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮችና ለማያግባቡ ጉዳዮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከህዝብ የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች ሲያደራጅ ቆይቶ በሐምሌ ወር ለሚጀምረው ዋናው የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ ስምንት አጀንዳዎችን ለይቶ ይፋ አድርጓል።

የምክክር አጀንዳዎቹ ይፋ መደረጋቸውን ተከትሎ ኢዜአ በቦንጋ ከተማ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳዎቹ በጥልቅ እይታ ተደራጅተው የቀረቡ ሀገራዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለምክክር የተለዩት አጀንዳዎች ለቆዩ ችግሮችና ለአለመግባባቶች ምክንያት ሆነው የቆዩ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እንደሆኑም ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ብርሃኑ ገብሬ እና ወጣት አካሉ ወልደኢየሱስ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ባለፉት ዓመታት ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ አጀንዳ በማሰባሰብና በመለየት ላደረገው ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ከህዝብ የቀረቡ በርካታ አጀንዳዎችን አደራጅቶ ለምክክር ያቀረባቸው ስምንት አጀንዳዎች ሀገር መክራ መፍትሄ ልታመጣባቸው የሚገቡ አጀንዳዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኮሚሽኑ ተለይተው ለምክክር የቀረቡ አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮችና ለአለመግባባት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በጋራ መክሮ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ለሁሉም የምትመች ሀገር መገንባት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል። 

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት መምህር አገኘሁ ተፈሪ እና ወይዘሮ ፍሬሕይወት ገዛኸኝ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን መሆን ከምክክር የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አንስተው፣ በኮሚሽኑ ተለይተው በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ መክረን ችግሮቻችንን መፍታት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለዋናው የምክክር ጉባኤ ለይቶ ያቀረባቸው የምክክር አጀንዳዎች የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌደራል ከተሞች ጉዳይ፣ የሐይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስና እና መልካም አሥተዳደር እንዲሁም የሰላም ግንባታ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም