በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት 31 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት 31 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ይለማል
አምቦ ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር እርሻ 31 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ የማልማት ስራ መጀመሩን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዞኑ ኢሉ ገላን ወረዳ የ2018/19 የምርት ዘመን ሩዝን በኩታ ገጠም የማልማት ስራ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እንደገለጹት፤ በክልሉ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ተቀርጾ ወደ ስራ ከገቡት 33 ኢኒሼቲቮች መካከል የሩዝ ምርት አንዱ ነው።
የሩዝ ምርት በዞኑ በስፋት ያልተለመደ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ህብረተሰቡ በአንድነት በኩታ ገጠም ተደራጅቶ ወደ ስራው መግባቱን ጠቅሰዋል።
ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ የሚችል በመሆኑ፣ በ36 ሄክታር መሬት ላይ የሩዝ ዘር መዘራት መጀመሩን ገልጸዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲሳ ሀይሉ በበኩላቸው በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለመሸፈን ታቅዷል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ31 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት በሩዝ ምርት ለመሸፈን ታቅዶ ስራው ተጀምሯል ብለዋል።
የኢሉ ገላን ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በንቲ በበኩላቸው፣ የወረዳው አርሶ አደሮች የሩዝ ምርት የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን እየተላመዱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በወረዳው በ2018/19 የምርት ዘመን 5 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ምርት ለመሸፈን ታቅዶ፣ የግብርና ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮቹ በማቅረብ ዘር የመዝራት ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል ዘውዱ ዘነበ፤ የሩዝ ሰብልን በኩታ ገጠም መዝራት ከጀመሩ አራት ዓመታት እንደሆናቸው ገልጸው፣ ቀደም ሲል ከሄክታር አነስተኛ ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በግብርና ባለሙያዎች በሚደረግላቸው ሙያዊ ድጋፍ ታግዘው ከአንድ ሄክታር ማሳቸው እስከ 80 ኩንታል የሩዝ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።