ቀጥታ፡

የምክክር አጀንዳዎቹ ለሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት የሚያኖሩ ናቸው-ምሁራን

ጅማ ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተለይተው የቀረቡ የምክክር አጀንዳዎቹ ሲንከባለሉ ለቆዩ ችግሮች መልስ ለመስጠት የሚያስችሉና ለሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት የሚያኖሩ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ዜጎች ባማከለ እና አካታች በሆነ መልኩ በማወያየት፣ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ግብዓት የሚሆኑ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ አድርጓል። 

የሀገር ግንባታ ጉዳይ፤ የመንግስት አደረጃጀትና ሥርዓት ጉዳይ፤ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬድዋ ከተሞች ጉዳይ፤ የሐይማኖት ጉዳዮች፤ የተቋማት ግንባታ የህግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፤ ሙስና እና የመልካም አስተዳዳር ጉዳዮች እንዲሁም የሰላም ግንባታ ጉዳዮች በኮሚሽኑ የተለዩ የምክክር አጀንዳዎች መሆናቸው ይታወቃል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረጋቸው የምክክር አጀንዳዎች የሀገርና የዜጎችን የወደፊት ዕጣ ፈንታን የሚወስኑ መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና አስተዳደር ኮሌጅ መምህር ቃሶ ጠሀ፤ ኮሚሽኑ ላለፉት አራት አመታት ያከናወናቸው ተግባራት የሚያስደንቁና የሚያስመሰግኑት መሆናቸውን አንስተዋል።

የተለዩት የምክክር አጀንዳዎች በጥቅል እይታ የተለዩ መሆናቸውን አንስተው ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀምና በሰከነ አግባብ በመምከር ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ይገባል ብለዋል።

የበርካታ ሀገራት መሠረታዊ ችግሮቻቸው የተፈቱት በጥንቃቄ ተለይተው ለውይይት በመቅረባቸው መሆኑን አስታውሰው ኢትዮጵያም ይህንን እድል መጠቀም ይገባታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሺዎች ከሚቆጠሩ አጀንዳዎች በጥንቃቄ በመለየት ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ለይቶ ማቅረቡን አድንቀው በጥልቀት ልንመክርባቸውና ችግሮችንም ልንፈታባቸው ይገባል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሕግ እና አስተዳደር ኮሌጅ መምህርና መልካም አስተዳደር እና ልማት ጥናት ተመራማሪ ግርማ ደፈረ (ዶ/ር)፤ እውነተኛ ውይይት የአንድ ጊዜ ክስተት ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ይህን በሚገባ በመረዳት ለምክክር አጀንዳዎችን ለይቶ ማቅረቡን አድንቀው ይህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ፣ የሀገረ መንግስት ግንባታ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ጭምር ብዙ ስብራቶች ያሉት መሆኑን አንስተው በምክክር የሚጠገንበት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ጉዳይ መክረን ዘላቂ መፍትሄ በማምጣት ለሁላችንም የምትመች ጠንካራ ሀገር መገንባት የዚህ ትውልድ አደራና ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ አጽኖት ሰጥተዋል።

የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም