በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለተከልናቸው ችግኞች ዘላቂ እንክብካቤ እናደርጋለን - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለተከልናቸው ችግኞች ዘላቂ እንክብካቤ እናደርጋለን
ሐረር ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተሳታፊዎች በመርሃግብሩ ከችግኝ ተከላ ባሻገር ለችግኞች ዘላቂ እንክብካቤ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ መነቃቃትና ህዝባዊ ተሳትፎ እየተከናወነ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች፣ ዋናው ትኩረታቸው ችግኝ መትከል ላይ ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በአግባቡ ተንከባክቦ ማሳደግ ላይ ነው።
ነዋሪዎቹ ለአካባቢ ጥበቃና ለቀጣዩ ትውልድ ያለባቸውን አደራ ለመወጣት በየዓመቱ የሚያደርጉትን የችግኝ ተከላ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ፣ ከተከላው ማግስት ጀምሮ ላለው የክትትል፣ የውሃ አቅርቦትና የጥበቃ ሥራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ይበልጥ ጠንክረው እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዘመቻው ተሳታፊዎች መካከል ፋዮ ሙክታር እንዳለችው፤ አረንጓዴ አሻራ የአካባቢን ልምላሜ እንድናይና ነፋሻማ አየር እንድናገኝ አስችሏል።
"ችግኝ ተክሎ አለመንከባከብ ልጅ ወልዶ አለማሳደግ" መሆኑን በመጠቆም በመርሃ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራውን እንደሚያጎለብቱ ተናግራለች።
ኦሪት አብዲ በበኩሏ፤ በክረምት የምናከናውነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራ ሐረርን አረንጓዴ በማልበስ ውበቷ እንዲጨምር አድርጓታል ብላለች።
በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራን እቅድን መሰረት ባደረገ መልኩ ለማከናወን መዘጋጀታቸውን አክላለች።
ወጣት ረስተም ኡመር በበኩሉ፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚከናወነው የችግኝ ተከላ ከሀገሪቱ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራትም እንድንተርፍ ያስቻለ ነው ብሏል።
በተለይም በመርሃ ግብሩ ወጣቶች በንቃት እየተሳተፍን እንገኛለን ብሏል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሐረማያ ሃይቅ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም መምህር ዲኔ ረሺድ እንዳሉት፤ በተፋሰሶች ላይ በአረንጓዴ አሻራ የሚከናወኑት የችግኝ ተከላ ስራዎች አፈር መሸርሸርን በመከላከል ውሃ ወደ ከርሰ ምድር እንዲገባ እያስቻለ ነው።
ይህም ለዓመታት ደርቆ የነበረው የሐረማያ ሃይቅ እንዲመለስ ያስቻለው የአረንጓዴ አሻራ ስራ ንቅናቄ ውጤት መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ ላይ በአንድነት ተሳትፎ እያደረገና አካባቢውንም እየለወጠ መሆኑንም አክለዋል።
በሐረሪ ክልል የዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትናንት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በተገኙበት መጀመሩ ይታወቃል።