በኮሚሽኑ ተለይተው የቀረቡ የምክክር አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኮሚሽኑ ተለይተው የቀረቡ የምክክር አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው
አሶሳ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በኮሚሽኑ ተለይተው የቀረቡ የምክክር አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሚያካሂደው ታሪካዊ የምክክር ጉባዔ ላይ ውይይት የሚደረግባቸውንና ከሕዝብ የቀረቡ አጀንዳዎችን በይፋ ማሳወቁ ይታወቃል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሕብረተሰቡ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በመለየትና መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
የተለዩት አጀንዳዎች ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማእከል ያደረጉና ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸው፤ ለሂደቱ ውጤታማነት የሁሉም ወገን ትብብርና ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ሙሳ ኡመር፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚያካሂደው ጉባዔ የምክክርን አስፈላጊነት በተግባር የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የሁሉንም ዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲያቀርቡ ዕድል በማመቻቸት የምክክር ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በኮሚሽኑ የቀረቡ የምክክር አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ እንደሚሆኑ አምናለሁ ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪ አቶ ተፈሪ ቡልቹ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከህዝብ የቀረቡለትን አጀንዳዎች በመለየትና በጥልቀት በማጤን ለዋናው ምክክር ያቀረባቸው ስምንት የምክክር አጀንዳዎች ሁሉንም ማእከል ያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክክሩ የቀረቡት የመወያያ አጀንዳዎች ጥቅል ሆነው በውስጣቸው በርካታ ጉዳዮችን ያካተቱ መሆናቸውን አንስተው በአግባቡ ከመከርንባቸው ለጋራ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጡ ይሆናሉ ብለዋል።
በኮሚሽኑ የተለዩ አጀንዳዎች በየአካባቢው በተካሄዱ የህዝብ ውይይት መድረክ ላይ የተነሱ እና የሁሉንም ማህበረሰብ ክፍሎች ያካተቱ ናቸው ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዝሁር ከማል ናቸው።
የምክክሩ አጀንዳዎች ሁሉን አቀፍ ጉዳዮችን የያዙ ለሀገር ልማት፣ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ ለህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ጠንካራ መሰረት የሚያኖሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መምህር ደረጀ ደለና፤ በኮሚሽኑ የተለዩት ስምንቱ አንኳር የሆኑ አጀንዳዎች በውስጣቸው በርካታ ሃሳቦችን የያዙ መሆናቸውን ገልጸው በአግባቡ ከመከርንባቸው ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
የሀገር ግንባታ ጉዳይ፤ የመንግስት አደረጃጀትና ሥርዓት ጉዳይ፤ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬድዋ ከተሞች ጉዳይ፤ የሐይማኖት ጉዳዮች፤ የተቋማት ግንባታ የህግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፤ ሙስና እና የመልካም አስተዳዳር ጉዳዮች እንዲሁም የሰላም ግንባታ ጉዳዮች በኮሚሽኑ የተለዩ የምክክር አጀንዳዎች መሆናቸው ይታወቃል።