የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ነገሌ አርሲ በ57 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ46 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ36ኛ ሳምንት ከሊጉ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና ጋር አንድ አቻ የተለያየው ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በተመሳሳይ በ36ኛ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ለማስመዝገብ ይፋለማል።
ነገሌ አርሲ ካሸነፈ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የማጠናቀቅ እድሉን የበለጠ ያሰፋል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ፋሲል ከነማ በ52 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ50 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ድል የቀናው ፋሲል ከነማ በአሸናፊነት ጉዞው ለመቀጠል ይጫወታል።
በ36ኛ ሳምንት ከምድረ ገነት ሽሬ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና መቀሌ 70 እንደርታን ያገናኛል።
ኢትዮጵያ ቡና በ47 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ መቀሌ 70 እንደርታ በ37 ነጥብ 19ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ቡናማዎቹ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ድል አልቀናቸውም። ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እያደረገ ባለው ትግል በዋጋ የማይተመን ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
አርባምንጭ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ከሊጉ መውረዱ የተረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ በ35 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ42 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ካሸነፈ በሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት እስከ ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው፣ የፋሲል ከነማው ታምራት እያሱ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ናትናኤል ዳንኤል በተመሳሳይ 14 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ይገኛል።