ቻይና ለብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ለብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):- ቻይና በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላሸነፈው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሚመራው የብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፋለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በዚህም መሠረት የብልጽግና ፓርቲ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 501 መቀመጫዎች መካከል 438ቱን አገኝቷል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉዎ ጂያኩን በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ቻይና የኢትዮጵያ ታማኝና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋር (all-weather strategic partnership) መሆኗን ገልጸዋል።
ቻይና ኢትዮጵያ የራሷን ተጨባጭ ብሔራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የልማት ጎዳና እንድትከተል የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥልና በቀጣይም የላቀ ሀገራዊ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ያላትን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የደረሱባቸውን ታሪካዊ ስምምነቶች እንዲሁም በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) ጉባኤ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በሁሉም ዘርፎች ያለውን ትብብር ይበልጥ በማጠናከር ለሁለቱም ሀገራት ሕዝቦች የላቀ ጥቅም ለማስገኘት እንዲሁም በቻይና-አፍሪካ እና በደቡብ ንፍቀ ክበብ (Global South) ሀገራት መካከል ያለውን አንድነትና ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ቻይና አበክራ እንደምትሠራ ቃል አቀባዩ መናገራቸውን የዥንዋ የዜና ወኪል ዘገባ ያመለክታል።