የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የዜጎችን መብት በማስከበር አስተዳደራዊ በደልን ለመከላከል የጀመረውን ሥራ ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የዜጎችን መብት በማስከበር አስተዳደራዊ በደልን ለመከላከል የጀመረውን ሥራ ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የዜጎችን መብት በማስከበር አስተዳደራዊ በደልን ለመከላከል የጀመራቸውን ተግባራት ማጠናከር እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ምክር ቤቱ ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።
በዚሁ ወቅት ዋና እምባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ በአፈፃጸም ሪፖርታቸው፤ የፍትሕ መጓደልንና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን ቀድሞ በመከላከል የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ፤ በቅሬታ አፈታት፣ መልካም አስተዳደር ጉድለት ቅድመ መከላከል ተግባራት ተጠናክረው በሚቀጥሉበት ዙሪያ ጥያቄ አንስተዋል።
ዋና እምባ ጠባቂ ስመኝ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራርያ፤ በተቋማት ላይ ምርመራ በማድረግ የዜጎችን የአስተዳደር በደል የሚያስቀር አቅም እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ 108 የመንግሥት ተቋማት ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ በ201 መስሪያ ቤቶች ላይ ተፈፃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
የዲጂታል አሰራሮችና በ9503 የአቤቱታ መቀበያ ነፃ መስመር መረጃ በመሰብሰብ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መፈጠሩን አብራርተዋል።
በቀጣይም ምክር ቤቱ የሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦች በግብዓትነት በመጠቀም የተሻለ አቅም ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፤ በተቋማት ላይ የሚደረግን ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር አስተዳደራዊ በደሎችን ለመከላከል የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዓለም አቀፍ ልምዶችና ተሞክሮዎችን በመቀመር ጭምር የዲጂታል መረጃ መሰብሰቢያ አሰራሮችን በማጎልበት በዜጎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ በደሎችን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አስተዳደራዊ በደሎችን ቀድሞ በመከላከል የተከናወኑ ተግባራትም የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ስብሰባው የመረጃ ነፃነት አዋጅን እና የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አፅድቋል።