ብቁ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው የዘመናዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
ብቁ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው የዘመናዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ይጠናከራል
ድሬዳዋ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):-የነገዋን ኢትዮጵያ በአንድነት የሚገነባ ብቁ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው የዘመናዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
በድሬዳዋ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ለሚገነባው ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።በጠቅላላው10 ሄክታር መሬት ላይ ለሚገነባው የአዳሪ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታውን ያስጀመሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።
ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሁሉም ክልሎች አንድ አንድ ለመገንባት ታቅዶ ወደሥራ ተገብቷል።
በትምህርት ቤቶችም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ሥራ አምና በአምስት ክልሎች መጀመሩን አስታውሰው ዘንድሮ ድሬዳዋን ጨምሮ በአራት የክልል ከተሞች የግንባታ ሥራ ይጀመራል ብለዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለፃ እየተገነቡ በሚገኙት ዘመናዊ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሲጠናቀቁ ከመላው አገሪቱ የሚሰባሰቡ ውጤታማ ተማሪዎች የተለያዩ የክህሎትና የቀለም ትምህርት ይቀስሙባቸዋል።
ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የዲጂታል፣ የግብርናና ሌሎች ሙያዊ ክህሎትን በተግባር ጭምር ተምረው የሚወጡበት ነው ብለዋል።
ዛሬ በድሬዳዋ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ግንባታው የተጀመረው ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አመልክተዋል።
አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የነገዋን ኢትዮጵያ በህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚገነቡ ብቁና ታታሪ ወጣቶች የሚፈሩባቸው መሆኑንም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ የትምህርት ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ በራሱ በጀት አዳሪ፣ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መገንባት በመጀመሩ አመስግነዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የትምህርት ፍትሃዊ ተደራሽነትና ጥራትን ከማሳደግ ባሻገር አስተዳደሩ ያለውን ውስን በጀት ሌሎች የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እንዲያውል ያስችለዋል ብለዋል።
ዛሬ ግንባታው የተጀመረው አዳሪ ትምህርት ቤት በሚፈለገው ጊዜና ጥራት ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ በአስተዳደሩ በኩል የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።