ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ ስትራቴጂክ አጋርነት እየተሸጋገረ ነው 

አዲስ አበባ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ ስትራቴጂክ የዲፕሎማሲ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑን በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን ገለጹ።

በኢትዮጵያ እና እንግሊዝ መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማሳደግ የተዘጋጀው የኢትዮ-እንግሊዝ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም 2026 በለንደን ከተማ ተካሂዷል።


 

በዩናይትድ-ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያና እንግሊዝ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ዘመናትን የተሻገር ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት ናቸው ብለዋል።

የሀገራቱ መልካም ግንኙነትም የንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትብብርን በማሳደግ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ጭምር እያጠናከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ ስትራቴጂክ የዲፕሎማሲ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረምም የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ አጋርነትን ለማጎልበት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የብዝኅ ዘርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ለሀገራቱ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩንም አንስተዋል።

በቀጣይም የሀገራቱን ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር የበለጠ በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲም የሁለቱን ሀገራት የንግድ፣ የኢንቨስትመንትን፣ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ስትራቴጂክ አጋርነት ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በፎረሙ ላይ የሀገራቱ የፖሊሲ አውጪ ሙያተኞች፣ ባለሃብቶችና የተለያዩ ተቋማት ጋር የሃሳብ ልውውጦች መደረጋቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም