የኢትዮጵያ የዲጂታል እመርታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲጂታል እመርታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፍ እመርታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
በኢትዮጵያ እና እንግሊዝ መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማሳደግ የተዘጋጀው የኢትዮ-እንግሊዝ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም 2026 በለንደን ከተማ ተካሂዷል።
የኢትዮ-እንግሊዝ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ጎን ለጎንም በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሄዷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በዚሁ መድረክ፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ኢትዮጵያ ስኬታማ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓን አስረድተዋል።
የግብርና፣ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ዘርፍ የሚያስመዘግቡትን እመርታዊ ዕድገትም ዲጂታል ቴክኖሎጂ እያሳለጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አምስቱ የብዝኅ ኢኮኖሚ ዕድገት መሰሶዎችም በዲጂታል መሰረተ ልማት ታግዞ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ዘርፍ የኢትዮጵያ ብዝኅ ኢኮኖሚ መሰሶ አካል መደረጉም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን አስረድተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የዲጂታላይዜሽን ሂደት ዋና ስትራቴጂ ደረጃዎችን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር እንዳስቻለም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የበለፀጉ ሀገራት ያለፉበትን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድና ከነባራዊ አውድ ጋር በማጣጣም በወሳኝ የሽግግር ሂደት ላይ እያለፈች መሆኗን ገልጸዋል።
የዲጂታል ዘርፍ እመርታም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
በፓናል ውይይቱ አወያይ የነበሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዘመዴነህ ንጋቱ እንዳሉት፤ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአስደናቂ የዕድገት ምዕራፍ እያለፈች ነው።
በዚህም በመሰረተ ልማትና በዲጂታል ዘርፍ የተመዘገበው እመርታዊ ውጤትም ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አስቻይ የትራንስፎርሜሽን ምኅዳር መፍጠሩን አስገንዝበዋል።