ቀጥታ፡

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የወል ትርክት በሚገነባ እና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ተግባራዊ ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የወል ትርክትን በሚገነባ እና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትርና የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገለፁ።

የብልፅግና ፓርቲ አባል የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የሰባተኛው የጠቅላላ ምርጫ የማጠቃለያ ሪፖርት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትርና የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ማጠቃለያ እና ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በማጠቃለያቸው ለቀጣይ ተልዕኮዎች ስኬት የአመራርና አባላትን ቁርጠኝነት ማጥራት እንዲሁም ተቋማዊ ኃላፊነቶችን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለቀጣዩ ከባድ ተልዕኮ ግልፅነትና ዝግጁነት ያለው የሰው ኃይል ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸው፤ አመራሩ ለዚህ ዝግጁ መሆን አለበት ብለዋል።

የፓርቲው ማኒፌስቶ በየሚኒስቴሩ ዕቅድ ውስጥ ተካቶ መተግበር እንዳለበት ተናግረው፤ የፌዴራል ተቋማት ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚያመነጩ፣ በጀትን የሚመሩ አጀንዳ ፈጣሪዎች በመሆናቸው ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በየተቋማት ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተለይተው መፈታት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዘንድሮው የፌዴራል ተቋማት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ ለየት ባለ መልኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በዚህም ትርክት ግንባታን፣ የወል ትርክትን፣ ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ በአፅዕኖት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ በሚል መሪ ሐሳብ ህዝብን ያሳተፈና ዘላቂ የሀገር ግንባታን የሚያረጋግጥ መጠነ-ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ 

ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ከዳር ለማድረስ አካታችነትን፣ ሚዛናዊነትን፣ የሀሳብና የባህል ልዩነቶችን ማክበርን እንዲሁም በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም