ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በስኬት ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ ነው

ወልቂጤ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በስኬት ለማጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅትን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተዘጋጀው የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ፈተናውን በስኬት ለማጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት መወጣት ይኖርባቸዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ ከ31 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና የሚቀመጡ ሲሆን፣ ፈተናው በክልሉ በተዘጋጁ 34 ማዕከላት ይሰጣል ብለዋል።

ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 18 ሺህ 827 ተማሪዎች ፈተናውን በኢንተርኔት አማካኝነት የሚወስዱ ሲሆን፣ ለዚህም ስኬት ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ አበበ ሎላሞ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ተፈታኝ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድና ለማስፈተን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።


 

የኢትዮ ቴሌኮም የሆሳዕና ዲስትሪክት ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አለማየሁ አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኦንላይን ፈተና በሚሰጥባቸው ማዕከላት ላይ አስተማማኝ የኔትወርክ ዝርጋታ መከናወኑን አረጋግጠዋል።

በፈተና ወቅት የኢንተርኔት መቆራረጥን ጨምሮ ከቴሌኮም አገልግሎት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችግሮች ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል።

የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ አቶ ፍሬው ገዛህኝ፣ ተፈታኞች ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲወስዱ በየማዕከላቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ማስፈጸሚያና የኦንላይን ፈተና ዕቅድ ዝግጅት ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል።

በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የልዩ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም