የሀረር ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ማስፋፊያ የክልሉን የሜዲካል ቱሪዝም የሚያጎለብት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀረር ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ማስፋፊያ የክልሉን የሜዲካል ቱሪዝም የሚያጎለብት ነው
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 18/2018/(ኢዜአ) ፦ የሀረር ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክት የክልሉን የሜዲካል ቱሪዝም ይበልጥ የሚያጎለብት ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የሀረር ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ማስፋፊያ የግንባታን የአፈጻጸም ሂደት ተመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው የሪፈራል ሆስፒታሉን ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑ ማየታቸውን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም የህክምና አገልግሎቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በክልሉ ለጤና አገልግሎት ተደራሽነት ልዩ ትኩረት ተሰቶት ወደ ስራ መገባቱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የሆስፒታሉ ማስፋፊያም በክልሉ በጤና ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል።
በተለይ ሀረር ጎረቤት አገራትን ጨምሮ ከአጎራባች ክልሎች ለህክምና የሚመጡ በርካታ ተገልጋዮች የሚስተናገዱባት የሜዲካል ቱሪዝም ከተማ መሆኗን ጠቅሰው የሆስፒታሉ ማስፋፊያ የሜዲካል ቱሪዝሙን ይበልጥ የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ጥሩ በሚባል አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ በማመላከት በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።