የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ እመርታ ለውጭ አልሚ ባለሃብቶች ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳርን ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ እመርታ ለውጭ አልሚ ባለሃብቶች ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳርን ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት እመርታ ለውጭ አልሚ ባለሃብቶች ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳር መፍጠሩን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
በኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብርን ለማሳደግ የተዘጋጀው የኢትዮ-እንግሊዝ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም 2026 በለንደን ከተማ ተካሂዷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ አምራች የሰው ኃይል፣በዓመት ከሶስት ጊዜ በላይ የሚያመርት መሬትና የብዝኅ ጸጋ ምድር ናት ብለዋል።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ተግባራዊ የተደረገው የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫም በግብርና፣ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚም በሁሉም ወቅቶች ዘመናዊ አስተራረስ ምኅዳርን በማስፋት የኢንዱስትሪ ሽግግርን እያፋጠነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ለማሻሻል ተግባራዊ የሆኑ የሕግና የአሰራር ማሻሻያዎችም ለውጭ ባለኃብቶች አስቻይ ምኅዳር መፍጠሩን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት አቅም የምግብ ሉዓላዊነትን በሚያረጋግጥ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እየተመራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
የእንግሊዝ አልሚ ባለሃብቶችም የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳር መጠቀም የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩንም አብራርተዋል።