ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ ያገኙት መቀመጫ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጠናከር ዕድል ይሰጣል - ኢዜአ አማርኛ
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ ያገኙት መቀመጫ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጠናከር ዕድል ይሰጣል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ ያገኙት መቀመጫ፣ ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጠናከር ዕድል የሚሰጥ መሆኑን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች የተገኘውን ውጤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህም የብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤቶች አብላጫውን መቀመጫ ማግኘቱንና በምክር ቤቶቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መቀመጫ ማግኘታቸውን አረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር)፤ ምክር ቤቱ የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት ዕድል ማግኘቱን ገልጸዋል።
ከሌላው ጊዜ ይበልጥ የሕብረተሰብ ድምፅ የሚሰማበትና ለኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጠናከር በር የሚከፍት መሆኑንም ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ የታየበትና ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጭ የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ አባል ኢንጅነሪ ስለሺ ኮሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያስችል ዝግጅት አስቀድሞ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋቱን ተከትሎ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚዛናዊነት ላይ የተመሠረተ ፉክክርና ትብብር እንዲያደርጉ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ዲሞክራሲን ለማጎልበት እና ሀገርን በጋራ ለመገንባት ያለውን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ከመረጣቸው ሕዝብና ከፓርቲያቸው ጋር በመሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተገቢው ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት የሕዝቡን ሰላም ማረጋገጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያመነጩ ፖሊሲዎችን ገቢራዊ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡