የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች በተቀናጀ አግባብ እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች በተቀናጀ አግባብ እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች በተቀናጀ አግባብ እየተከናወኑ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 13ኛውን የትምህርት ጥራት ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል፡፡
በጉባኤው ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች በተቀናጀ አግባብ እየተከናወኑ ነው።
ሚኒስቴሩ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲዎችን በመቅረፅና በመተግበር፣ ሀገር አቀፍ የብቃት ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ አጠቃላይ የትምህርት አዋጅ እንዲወጣ በማድረግና ሌሎች የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ከነዚህ ማዕቀፎች በመነሳት የትምህርት ቤት አመራር ብቃትና ተነሳሽነት የማጎልበት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሀገር የተወጠኑ የትምሀርት ጥራት ሥራዎችን ያለመምህራን ተሳትፎ ማሳካት የማይቻል በመሆኑ ሚኒስቴሩ ከመምህራን ማህበር ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
መምህራን የሚያቀርቧቸው በጥናትና ምርምር የተደገፉ የመፍትሔ ሀሳቦች የተጀመረውን የለውጥ ሥራ በሚያግዝ መልኩ በግብዓትነት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው፤ በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት እየተወሰዱ ባሉ እርጃዎች ላይ የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በለውጥ ሥራዎች ላይ ተባብሮ ከመስራት ባሻገር የመምህራን መብትና ጥቅሞች እንዲጠበቁ ከክልሉ መምህራን ማህበር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ፤ጥራት ያለው የትምህርት አሰጣጥ እንዲኖር በማድረግ በዕውቀት ፣ ክህሎትና አመለካከት የበለፀገ ትውልድ ማፍራት ማህበሩ በቀዳሚነት ከያዛቸው አላማዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማህበሩ መምህራንን በብቃትና በአመለካከት የተሻሉ እንዲሆኑ በማድረግ ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልድ ማድረስ እንዲቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በተለያዩ መድረኮች ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ የማገዝ ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ኢያሱ ፍቅሬ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመቀናጀት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የፌዴራልና የክልል መምህራን ማህበራት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ጥሪ የተደረገላቸው አካላት የተገኙ ሲሆን የትምህርት ጥራትን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍም ቀርቧል፡፡