ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚፃረሩ ኃይሎችን ስጋት የሚቀለብስ ዘመኑን የዋጀ አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት ተገንብቷል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚፃረሩ ኃይሎችን ስጋት የሚቀለብስ ዘመኑን የዋጀ አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት መገንባቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ጀነራል አለምእሸት ደግፌ አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ "የኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነት ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች" በሚል መሪ ሀሳብ ዓመታዊ የምክክር ጉባዔ እያካሄደ ይገኛል።


 

ጀነራል አለምሸት ደግፌ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ዕድገትን በሚያፋጥን ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ላይ ትገኛለች።

የሀገሪቱን ዕድገት ለማደናቀፍ የሚሹ ጽንፈኛና ሽብርተኛ ኃይሎች የሚያደርጉት ከንቱ ሙከራም በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሰላም ወዳዱ ህዝብ እየመከነ መሆኑን ገልጸዋል።

ጽንፈኝነትና አክራሪነት የሀገር ልማትና አንድነት ጸር መሆኑን የጠቀሱት ጀነራል አለምእሸት፤ የጥፋት እንጂ የዓላማ አንድነት የሌላቸው ኃይሎች የኢትዮጵያ ዳግም ስጋት እንዲሆኑ ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ሰላምና ሉዓላዊ ክብር በማፅናት ዕድገቷን ማፋጠን የሁሉም ዜጋ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዓለማችን ከነጠላ ልዕለ-ኃያል ወደ ብዙ ዋልታ የሽግግር ሂደት ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ጀነራል አለምእሸት፤ ሂደቱ በርካታ ውስብስብና አስቸጋሪ የፀጥታና የደህንነት ሁኔታዎችን ማስከተሉን አብራርተዋል።


 

አሁናዊው ቀጣናዊ ሁኔታ ዕድልም ስጋትም ይዞ የመጣ መሆኑን አመልክተው፤ እንደ ሀገር ዕድሉን ለመጠቀምና ስጋት ሆነው ለሚመጡ ችግሮች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ መከላከያ ሰራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።

ምስራቅ አፍሪካ የኃይል አሰላለፍና የመካከለኛ ኃይሎች ተፅዕኖ የሚታይበት ቀጣና መሆኑን ጠቅሰው፤ሁኔታዎችን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር በማስታረቅ በሳል ስትራቴጂን መከተል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተሰባብረው የነበሩ የሀገር ጠላቶች፣ ዛሬም ከብሔራዊ ጥቅሟ በተቃራኒ የቆሙ ኃይሎችን በማሰባሰብ ለዳግም የጥፋት ተልዕኮ እየተዘጋጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመከላከያ ሰራዊትም በሙሉ ወታደራዊ ዝግጁነት የተለመደውን የጀግንነት ገድል ለመፈፀም በቂ አቅም እንዳለውም አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ሃላፊ ጀነራል ይመር መኮንን በበኩላቸው፤ በወቅታዊና ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ከአፍሪካ ቀንድ የጋራ ሰላም፣ ተጠቃሚነትና ደህንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ያሉት ጀነራል ይመር፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት በማስቀጠል ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው መሰረታዊ አጀንዳ መሆኑን አስረድተዋል።

በጉባዔው ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር)፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዘሪሁን አበበና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም