ቀጥታ፡

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አግዟል-ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ   

ሀዋሳ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ ።

የሲዳማ ክልል የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የጨፋ ሲኔ ቀበሌ ተጀምሯል።

በመርሀ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት፤ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የግብርና  ምርታማነትን  በማሳደግ  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም አግዟል።

በዘንድሮ ክረምትም ተግባሩን ለማስቀጠል የችግኝ ተከላ እና የእንክብካቤ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከቡና፣ ፍራፍሬ ልማትና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በመተሳሰሩ የአርሶ አደሮች ምርታማነትና ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል።

የፍራፍሬ ልማቱን ከግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን የገበያ አማራጭ ማስፋት እንደተቻለም ጠቁመዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የተራቆቱ አካባቢዎች በአረንጓዴ አሻራ ልማት እንዲያገግሙ መደረጉ የተደራጁ ወጣቶች በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በሀዋሳ ከተማ አረንጓዴ አሻራን ከኮሪደር እና ከሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ጋር እንዲተሳሰር መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ ናቸው።


 

በዚህም የሃዋሳ ከተማን የብልጽግና ተምስሌት ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ተፈጥሮን በመጠበቅና በመንከባከብ ሥራ ህብረተሰቡን በንቃት ለማሳተፍ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ክፍለ ከተማ የጨፋ ሲኔ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሀኑ ሻፋሞ እንዳሉት፤ ቀደም ባሉት ዓመታት ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል። 


 

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በተሰጠ ትኩረት በአካባቢያቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማየታቸውን ገልጸው፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የመጣውን ውጤት ለማስቀጠል በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሀግብር ላይ መገኘታቸውን ተናግረዋል።  

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተፋሰስ ልማት ሥራ እርከን በመስራትና በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በተተከሉ ችግኞች የተራቆቱ መሬቶች ጭምር አገግመው ምርት መስጠት እንደቻሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም