በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል
ጋምቤላ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት፣ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሯን ጨምሮ የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በአቦቦ ወረዳ በሩዝ ሰብል ላይ እየተካሄደ ያለውን የምርምር ሥራ ዛሬ ጎብኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በወቅቱ እንዳሉት፤ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚቻለው የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ ሲቻል ነው።
ክልሉ ያለውን ሰፊ የመሬትና የውኃ ሀብት በምርምር መደገፍ ከተቻለ፣ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚተርፍ የሰብል ምርት ማግኘት እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ጋምቤላ ለሁሉም የግብርና ልማት ዓይነቶች ምቹ ሥነ-ምህዳር ያላት መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ዓለሚቱ፤ በተለይም የሩዝ ሰብል አዋጭ ተብለው ከተለዩት የሰብል ዓይነቶች በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሩዝ ልማትን ማዘመንና ማስፋፋት ከተቻለ ለአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ምርት ማግኘት እንደሚቻልም አክለዋል።
ልማቱን ለመደገፍ በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲና በቻይናው ዩናን ዩኒቨርሲቲ ቅንጅት እየተካሄደ ያለው የምርምር ሥራ የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽ፣ ለሥራው ስኬታማነት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የሥራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የታለመውን የግብርና ልማት ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለአርሶ አደሩና ለባለሀብቱ ተደራሽ ማድረግ ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በተለያዩ ተቋማት ትብብር በሩዝ ሰብል ላይ የተጀመረው የምርምር ሥራ ተስፋ ሰጪና ዘርፉን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የምርምር ሥራው እየተካሄደ ያለው ከቻይናው ዩናን ዩኒቨርሲቲ ጋር መሆኑን አስረድተዋል።
የአዲሱ የሩዝ ዝርያ ልዩ ባህሪያት መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ መሆኑ እንዲሁም በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ መመረቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
በሩዝ ዝርያዎቹ ላይ እየተካሄደ ያለው የማላመድ የምርምር ሥራ በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንደሚሆንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።